የአውሮፖ ህብረት "መጠነኛ መሻሻል" ታይቶበታል ባለው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ እንደሚወያይ ገለጸ
በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት በቀጣናው ያሉትን ችግሮች አወሳስቧቸዋል ብሏል ህብረቱ
የአውሮፖ ህብረት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ይመክራል
ህብረቱ ከሶስት ቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ በስብሰባው የሚካፈሉት ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ፣ሶማሊያ እና ሱዳን ጉዳይ ትኩረት እንደሚያደርጉ አስታውቋል።
የአውሮፖ ህብረት የውጭ ጉዳይ ም/ቤት በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ውሰጥ ስላለዉ ሁኔታ ትኩረት እንደሚያደርግና እንዲሁም በሱዳን የሲቪል መንግስት እንዲመሠረት እንደሚያበረታታ ገልጿል።
በለግዘንበርግ የሚካሄደውን ይህን ስብሰባ የሚመሩት የህብረቱ ምክትል ፕሬዝዳንትና የውጭ ግንኙነትና ፀጥታ ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፍ ቦሬል ናቸው።
ህብረቱ በአፍሪካ ቀንድ ያለው ሰብአዊ ችግር በግጭት እና በድርቅ ምክንያት መባባሱን ገልጾ፣ለዚህም ቲም ኢሮኘ በተለይም ለኢትዮጵያ፣ሶማሊያና ኬንያ ለምግብ እርዳታ የሚሆን 633 ሚሊዮን ዮሮ መመደቡን አስታውቋል።
በአፍሪካ ቀንድ ያለው ታሪካዊ ድርቅ ሁኔታውን አባብሶታል ብሏል ህብረቱ። ሽብርተኝነት እና የባህር ላይ ውንብድና በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና የሚስተዋሉ ተጨማሪ ችግሮች መሆናቸውንም መግለጫው ጠቅሷል።
በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት በቀጣናው ያሉትን ችግሮች አወሳስቧቸዋል ብሏል ህብረቱ።
ግብጽ ከአውሮፖ ህብረት ጋር ያላት ግንኙነት አዎንታዊ መሆኑን የገለጸው ህብረቱ በግብጽ የኮፕ27 መሪነት እና በዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ጉዳይ እንደሚመክር አስታውቋል።
ሚኒስትሮቹ በሚኖራቸው ስብሰባ መጠነኛ መሻሻል ታይቶበታል ያሉትን የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ያነሳሉ ተብሏል። ነገርግን በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም እንዲመጣ የኤርትራ ወታደሮች መውጣት፣ተኩስ አቁም ስምምነት፣ ሰብአዊ እረዳት አቅርቦት መዳረስ እና የሰብአዊነት ጥቃት ያደረሱ ተጠያቂ መሆን አለባቸው ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከህወሓት ጋር ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራ ቡድን መቋቋሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቅርቡ በተወካዮች ም/ቤት በቀረቡበት ወቅት ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ህወሓትም በኬንያ አመቻችነት ድርድር እንደሚኖርና ለዚህም ተደራዳሪ ቡድን ለመላክ መስማማቱን መግለጹ ይታወሳል።
የአፍሪካ ህብረትም ግጭቱ ሰለማዊ መፍትሄ እንዲያገኝ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፤በማድረግም ላይ መሆኑን እየገለጸ ነዉ።