በግላቸው 326 ገደማ የልብ ቀዶ ጥገናዎችን ያደረጉት ኢትዮጵያዊ ሐኪም
ዶ/ር ፈቀደ አግዋር በ4 ዓመታት ውስጥ ነው 326ቱን የልብ ቀዶ ጥገናዎች ያደረጓቸው
ከነዚም 290 ገደማዎቹ ሙሉ በሙሉ የልብና የሳንባን ስራ በማቆም የተሰሩ ናቸው
ከቶንሲል እና ተያያዥ ህመሞች ጋር በተያያዘ የሚመጡ በተለይም ቦርቀው ባልጠገቡ ህጻናት ላይ የሚያጋጥሙ የልብ ህመሞችን በማከም ይታወቃሉ፡፡
መሳቅ፤ መጫወትም ሆነ መቦረቅ አቅቷቸው ነጋቸው የጨለመባቸውን በርካታ ህጻናት ለመታደግ በመቻላቸውም ስማቸው በብዙዎች ይጠቀሳል፤ ኢትዮጵያው ልብ ቀዶ ጠጋኝ ሃኪም ዶ/ር ፈቀደ አግዋር፡፡
ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የልብ ቀዶ ጥገና ህክምና ታሪክ አዲስ ምዕራፍን ከፍተዋል የሚባልላቸው ዶ/ር ፈቀደ በግላቸው 326 ገደማ ቀዶ ጥገናዎችን ማድረጋቸውን ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
በገንዘብም ሆነ በአገልግሎት ለመገመት ሊያዳግት በሚችል ደረጃ በርካቶችን ረድተናል የሚሉት ዶ/ር ፈቀደ እነዚህን የብዙዎችን ህይወት የታደጉ ቀዶ ጥገናዎች በ4 ዓመታት ውስጥ ነው ያደረጉት፡፡
ከ326ቱ ውስጥ 290 ገደማዎቹ ቀዶ ጥገናዎች ሙሉ በሙሉ የልብና የሳንባን ስራ በማቆም የተሰሩ ናቸው፡፡ “27 አካባቢ ብቻ ናቸው ልብም ሳንባም ሳይቆም የሰራኋቸው” ሲሉም ነው የሚያስቀምጡት፡፡
ዶ/ር ፈቀደ እና የስራ ባልደረቦቻቸው በኢትዮጵያ እምብዛም ያልተለመደውን የህክምና ግልጋሎት ነው በመስጠት ላይ ያሉት፡፡ በዚህም ብዙዎች በሃገራቸው በቤተሰባቸው መካከል ሆነው በሚያግባባቸው ቋንቋ እየተነጋገሩ ርቀው ሄደው ሳይንገላቱ ህክምናውን ለማግኘት ችለዋል፡፡
ይህ መሆኑ በአገልግሎቱ በቶሎ አለመገኘት ምክንያት ሊጠፋ የሚችለውን ህይወት ከመታደግ፤ እንግልትና ድካምን ከማስቀረትም በላይ እንደ ሃገር ሊታጣ የሚችለውን የምንዛሬ ገንዘብ ያድናል፡፡
በራስ ሰው፣ አቅም እና ሃብት ታክሞ መዳኑም ቀላል አይደለም፡፡ ወደ ውጭ ሃገር የሄደው ታማሚ ሁሉ ድኖ ስለመመለሱም ዋስትና የለም፡፡
“እኔ ህንድ በምማርበት ጊዜ ወገኖቻችን የሚያሳልፉትን ይህን መከራ አይቻለሁ” የሚሉት ዶ/ር ፈቀደም “በሃገርህ መሬት በሃገርህ እውቀት ስትሰራ ይሄን ሁሉ ችግር ነው የምታስወግደው” ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ዶ/ር ፈቀደ “ዋናው ቁም ነገር የምትሰጠው ግልጋሎት ልብን ቀደህ ስትጠግን የምታስገኘው ውጤት ከዓለም ጋር ተቀራራቢ ነወይ? የሚለው ነው” ይላሉ፤ ሰዎች ወደ ውጭ ሄደው ከሚያገኙት ህክምና ያነሰ ውጤት የሚገኝ ከሆነ ወደ ውጭ ሄደው መታከማቸው ተገቢነት እንዳለው በመጠቆም፡፡
ውጤቴም፤ በፍጹም ከሌላው ዓለም የማይተናነስና ቆንጆ ውጤት ያለው ስራ ሰርተናልም ነው እውቁ ልብ ቀዶ ጠጋኝ ሃኪም የሚሉት፡፡ ይሄን ማንኛውም ሰው ስራዎቻቸውን በሚመለከት በዓለም አቀፍ መጽሄቶች (ጆርናልስ) ላይ ጭምር ከጻፏቸው ጽሁፎች አይቶ ለመረዳት እንደሚችል በመግለጽ፡፡
በአዲስ አበባ ተወልደው ያደጉት ዶ/ር ፈቀደ የሶስት ልጆች አባት ናቸው፡፡ በዚሁ በአዲስ አበባ፣ በጎንደር ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንዲሁም በህንድ ሃገር ቤንግሎር ተምረዋል፡፡
ዋና ስራዬ ቀዶ በመጠገን የሰዎችን ህይወት መቀየር ነው የሚሉት ዶ/ር ፈቀደ የሰራሁት ብዙ ነው ብዬ አላምንምና አሁንም ቀዶ ጥገናዎችን ማድረግ እፈልጋለሁ ሲሉ ይናገራሉ፡፡
የዶ/ር ፈቀደንና የባልደረቦቻቸውን ስራበሚመለከት አል ዐይን አማርኛ ለአንባቢዎቹ የሚያደርሰው ተከታይ ጥንቅር ይኖራል፡፡