“የኩላሊት እጥበት ተጠቃሚዎች በመድሃኒት ዋጋ ንረት ለችግር እየተጋለጡ ነው” የኩላሊት ህመምተኞች በጎ አድራጎት ድርጅት
ከዚህ ቀደም እስከ 130 ብር ሲሸጥ የነበረው መድሃኒት አሁን ላይ ከ900 እስከ 1000 ብር እየተሸጠ ነው ተብሏል
በግል ህክምና ማእከላት ለኩላሊት እጥበት አንድ ሰው በወር በአማካኝ ከ22 ሺህ እስከ 30 ሺህ ብር ለመክፈል ይገደዳል
የኩላሊት እጥበት ተጠቃሚዎች በመድሃኒት ዋጋ ንረት እንዲሁም በግል የህክምና ተቋማት የተጋነነ ዋጋ ለችግር እየተጋለጡ መሆኑን ይናገራሉ።
የኩላሊት እጥበት ተጠቃሚዎች አግልግሎቱን ለማግኘትም በመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ ባለው የማሽን ውስንነት በግል ተቋማት ከፍተኛ ዋጋ በመክፈል ለመገልገል እየተገደዱ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ የኩላሊት ህመምተኞች በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ ችግሩ በስፋት መኖሩን ለአል ዐይን አማርኛ አረጋግጠዋል።
አቶ ሰለሞን አሰፋ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ትንበያ በኢትዮጵያ 2 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ከኩላሊት ጋር የተያያዘ የጤና እክል እንዳለባቸው ያሳያል።
ከእነዚህም ውስጥ እስከ 80 ሺህ የሚደርሱት የኩላሊት እጥበት (ዲያላሲስ) የሚስፈልጋቸው መሆኑንም የዓለም ጤና ድርጅት ትንበያን መሰረት አድርገው ተናገረዋል።
አሁን ላይ ለኩላሊት እጥበት (ዲያላሲስ) የሚስፈልገው ማሽን እጥረት እና የመድሃኒት ዋጋ መናር ታማሚዎቹን ለችግር እየዳረገ መሆኑንም ነው ያስታወቁት፡፡
አቶ ሰለሞን እንዳሉት ፣ ከመድሃኒት ጋር ተያይዞ ታማሚዎች ከዚህ ቀደም ከ80 እስከ 130 ብር ሲገዙ የነበረውን መድሃኒት አሁን ላይ ከ900 እስከ 1000 ብር ለመግዛት እየተገደዱ ነው።
በተለይም ለደም ማቅጠኛ የሚውለው ‘ሄፓሪን’ የተባለው መድሃኒት ከኮቪድ-19 መከሰት ጋር ተያይዞ የፈላጊው እና አቅርቦት አለመመጣጠን በስፋት እንዳለም አቶ ሰለሞን ይናገራሉ።
በተለይም መድሃኒቱ በጥቁር ገበያ ላይ በከፍተኛ ዋጋ መሸጡ እና የግል የጤና ተቋማት እና መድሃኒት ቤቶች ያለ ከልካይ ዋጋ ጨምረው መሸጣቸው የዋጋ ንረቱን እንዳባባሰውም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የኩላሊት ህመምተኞች በጎ አድራት ድርጅት ከመድሃኒት ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ከጤና ሚኒስቴር ጋር ተቀራረቦ እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ከኩላሊት እጥበት (ዲያላሲስ) ጋር በተያያዘም አገልግሎቱ እስካሁን በ3 የመንግስት ሆስፒታሎች እና በ14 የግል የጤና ተቋማት እየተሰጠ መሆኑን አቶ ሰለሞን አሰፋ ይናገራሉ።
ምንም እንኳን በአዲስ አበባ በሶስት ሆስታሎች ማለትም በጳውሎስ፣ በዳግማዊ ሚኒሊክ እና በዘውዲቱ ሆስፒታሎች የኩላሊት እጥበት በነጻ ቢሰጥም፣ በመሳሪያ እጥረት የተነሳ በእድሉ መጠቀም የቻሉት 105 ሰዎች ብቻ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ቀሪዎቹ ታካሚዎች በግል የህክምና ተቋማት የዲያላሲስ አገልግሎትን ለመጠቀም ይገደዳሉ ያሉት አቶ ሰለሞን፣ ለዚህም አንድ ሰው በወር በአማካኝ ከ22 ሺህ እስከ 30 ሺህ ብር ለመክፈል እንደሚገደድም አንስተዋል።
ይህ ደግሞ በተለይ ፣ የመክፈል አቅም የሌላቸው ዜጎችን ለከፍተኛ ችግር እየዳረገ መሆንኑም ተናገረዋል።
አሁን ላይ ችግሩን ለማቅለል ከመንግስት ጋር የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን የሚያሱት አቶ ሰለሞን፣ 100 ማሽኖችን ከውጭ ገዝቶ ለማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል።
ማሽኖቹ በሚመጡበት ጊዜ እስከ 400 የሚሆኑ ዜጎች እፎይታ እንደሚያገኙ ገልጸው ፣ ከዲያላሲስ ጋር ተያይዞ ያለውን የዋጋ ንረት እንደሚያረጋጋም ይጠበቃል ብለዋል።
በተጨማሪም በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ እና የህክምና ትምህርት የሚሰጡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ባሉ ሪፈራል ሆስፒታሎች የኩላት እጥበት አገልግሎቱን ለማስጀመር እንቅስቃሴ ስለመጀመሩም ተናገረዋል።
ለኩላሊት እጥበት የሚያስፈልጉ ግብአቶች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።