የዓለም ጤና ድርጅት እውቅና አግኝተውም ሆነ ሳያገኙ ግልጋሎት ላይ የዋሉ በርካታ ክትባቶች አሉ
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ከባለፈው ዓመት ወዲህ የቫይረሱን ክትባቶች በማዘጋጀት ህይወትን ለመታደግ ብርቱ ጥረቶች ሲደረጉ ነበር፡፡
ለዚህም ሳይንቲስቶች ደክመዋል፣ በዘርፈ ብዙ የህይወት አድን ጉዳዮች ላይ ተመራምረዋል፤ በየቤተ ሙከራው ፈትሸው ውጤት አምጥተዋልም፡፡
የተመራማሪዎቹ ድካም ፍሬ አፍርቶም በተለያዩ ግዙፍ የዓለማችን ህክምና ተቋማት፣ መድሃኒት አምራች ኩባንያዎች ለመመረት የቻሉ ክትባቶችን ለማዘጋጀት ችለዋል፡፡
ብዙ ከተደከመባቸው ክትባቶች መካከልም 15 ያህሉ በአሁኑ ወቅት ውጤታማነታቸው ተረጋግጦ የዓለም ጤና ድርጅትን እውቅና አግኝተው ጥቅም በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡
ለዚህ የአስትራ ዜኔካ፣ የፋይዘር፣ የሲኖፋርም፣ የሞደርና፣ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን፣ የስፑትኒክ እና ሌሎች ክትባቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ሆኖም ይህ ሃገራት የራሳቸውን እውቅና ሰጥተው ግልጋሎት ላይ የሚያውሏቸውን ክትባቶች አያካትትም፡፡
ሌሎች በርከት ያሉ ክትባቶች በመዘጋጀትም ላይ ናቸው፡፡
ከነዚህ መካከል 184 ያህሉ በቅድመ ክሊኒካዊ የቤተ ሙከራ እና የእንስሳት የፍተሻ ሂደቶች ላይ ይገኛሉ፡፡
ከቫይረሱ የመከላከል አቅም እንዳላቸው የተረጋገጠላቸው 4 ክትባቶች ደግሞ በተለያዩ ደረጃዎች ለህዝብ ተሰራጭተው ተጽዕኗቸው እየተገመገመ ነው፡፡
እስካሳለፍነው እሁድ ግንቦት 15 ቀን 2013 ዓ/ም ድረስ በመላው ዓለም 1 ቢሊዬን 489 ሚሊዬን 727 ሺ 128 የኮሮና ክትባቶች ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡
በአጠቃላይ ከ167 ሚሊዬን በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠም ሲሆን የ3.4 ሚሊዬን ሰዎች ህይወት ማለፉን ደግሞ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃዎች አመልክተዋል፡፡