ከትንባሆ ጋር በተገናኘ በየዓመቱ 146 ሚሊየን አፍሪካውያን ህይወታቸውን ያጣሉ- የዓለም ጤና ድርጅት
በአፍሪካ ካሉ አምስት ወጣቶች አንዱ ትንባሆ ይጠቀማል ተብሏል
ትንባሆን ማቋረጥ በሽታዎች ከመከላከል በተጨማሪ እድሜ እንደሚጨምርም ነው የተገለጸው
ከትንባሆ ጋር በተያያዙ በሽታዎች “በየዓመቱ ከ146 ሚሊየን ገደማ አፍሪካውያን” ህይወታቸው እንደሚያልፍ የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ማትሺዲሶ ሞኤቲ፤ ትንባሆ በዓለም ላይ ለበርካታ ሰዎች ህልፈት መንስኤ መሆኑን ገልጸዋል።
“ሲጋራ ማጨስ በሰውነት ውስጥ ያሉትን ሁሉንም የሰውነት ክፍሎች የሚጎዳ ነው፤ በዚህም በየዓመቱም ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ህይወታቸው ያጣሉ”ም ነው ያሉት ዳይሬክተሯ።
ከሲጋራ በስተቀር የትንባሆ ምርቶችን መጠቀም በአፍሪካ እየጨመረ እንደመጣም ማትሺዲሶ ሞኤቲ አስረድተዋል።
ሞይቲ ትንባሆ ማጨስን ማቋረጥ ለካንሰር፣ ለልብ ህመም፣ ለደም መርጋት (ስትሮክ) እና ለሌሎች በሽታዎች የመጋለጥ እድልን ለመቀነስ የሚያስችል መንገድ ከመሆኑም በሻገር ዕድሜን ይጨምራል ብለዋል።
ትንባሆ ማቆም ከባድ ቢሆንም ዛሬ ለመጀመር ጥሩ ቀን ነው የሚል ምክር በማከልም ጭምር።
“የማይቻል ይመስላል ወይም ማጨስ ትልቅ ችግር የሌለው ይመስላል፤ ግን ዛሬ የምታደረጉት ነገር ለወደፊቱ የጤና ችግሮች እና የከፋ ሞት ሊያስከትል ይችላል”ም ነው ያሉት የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ማትሺዲሶ ሞኤቲ።
በአፍሪካ ካሉ አምስት ጎረምሳዎች አንዱ ትንባሆ ይጠቀማል ያሉት ዳይሬክተሯ “ይህ መለወጥ አለበት፤ ሲጋራ ማጨስን አቁሙና የመፍትሔው አካል ይሁኑ” ሲሉም ምክር ለግሰዋል።