የአፖሎ 11 አብራሪ የነበረው ጠፈርተኛው ማይክል ኮሊንስ በ90 ዓመቱ አረፈ
ለተልዕኮው ስኬት የጎላ አበርክቶ የነበረው ኮሊንስ ልክ እንደነ አርምስትሮን ሁሉ ጨረቃ ላይ እንዳላረፈ ይነገራል
ኮሊንስ አፖሎ 11 እነ ኒል አርምስትሮንግን እና በዝ አልድሪንን ጭና ወደ ጨረቃ ስትጓዝ የመንኮራኩሯ አብራሪ ነበር
ሶስት ጠፈርተኞችን ጭና እ.ኤ.አ በ1969 ወደ ጨረቃ የተጓዘችውን አፖሎ 11 መንኮራኩር አብራሪ የነበረው ማይክል ኮሊንስ በ90 ዓመቱ አረፈ፡፡
አፖሎ 11 እነ ኒል አርምስትሮንግን እና በዝ አልድሪንን ጭና ወደ ጨረቃ ስትጓዝ ኮሊንስ የመንኮራኩሯ አብራሪ ነበረ፡፡
እነሱ ጨረቃን በእግራቸው በረግጡ ጊዜም ኮሊንስ በመንኮራኩሯ መቆጣጠሪያ ክፍል ውስጥ በብቸኝነት የጨረቃ ምህዋርን ይዞር ነበር፡፡ ጨረቃ ላይ አላረፈም፡፡
24 ሰዓታትን በብቸኝነት እንዳሳለፈም የአፖሎ ተልዕኮ 50ኛ የስኬት ዓመት በታሰበበት በ2019 ላይ ተናግሯል፡፡
ጠፈርተኛ ባልደረቦቹ ጨረቃ ላይ አርፈው እሱ ባለማረፉ ይጸጸት እንደሆነ ደጋግሞ በብዙዎች የሚጠየቀው ኮሊንስ የህይወት ታሪኩን በከተበበት መጽሃፉ በሁኔታው እንደማይጸጸት ገልጿል፡፡
ይልቁንም የእሱን ሶስተኛነት ልክ እንደሌሎቹ ሁለት ጠፈርተኛ ባልደረቦቹ አስፈላጊ እና ወሳኝ እድርጎ እንደሚመለከትም ነው የጻፈው፡፡
ወደ ጠፈር በተደረጉ ሌሎች ጉዞዎች የተሳተፈው ኮሊንስ በህዋ ላይ የሚደረግ አሰሳ “የምርጫ ጉዳይ” እንዳልሆነ ደጋግሞ ይናገር እንደነበር የአሜሪካ የኤሮናቲካል እና ህዋ አስተዳደር ተቋም (ናሳ) ባወጣው የሃዘን መግለጫ አስታውቋል፡፡
ምንም እንኳን ተግባሩ አብረውት እንደተጓዙት ሌሎች ጠፈርተኛ ባልደረቦቹ ሁሉ የተገለጠና ብዙሃኑ የማያውቀው ቢሆንም ወደ ጠፈር ከተጓዙ ታሪክ ሰሪ አሜሪካውያን መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፍ መሆኑንም ነው ናሳ ያስታወቀው፡፡
አሜሪካ በዘርፉ የላቀ ስኬት ላይ እንድትደርስ የላቀ አበርክቶ ነበረውም ብሏል፡፡
ኮሊንስ በ1930 ነው በጣሊያን ሮም የተወለደው፡፡ አባቱ የጦር ጄነራል የነበረ ሲሆን እሱን በተዋጊ የአየር ኃይል ባልደረባነት ከአሜሪካ የጦር አካዳሚ ተመርቋል፡፡
ጠፈርተኛው እና የህዋ ጉዳዮች ተመራማሪው ኮሊንስ በካንሰር በሽታ ምክንያት በ90 ዓመቱ መሞቱን ቤተሰቦቹ አስታውቀዋል፡፡