ዩኤኢ የመጀመሪያዋን ሴት የአረብ ጠፈርተኛ የጠፈር ተመራማሪዎቿ አባል አድርጋ መረጠች
“ፕሮብ ሆፕ” የተሰኘችው የዩኤኢ መንኮራኩር በቅርቡ ማርስ ላይ በስኬት ማረፏ ይታወሳል
ዩኤኢ ሞሃመድ አል ሙላህ የተባለን ሌላ ጠፈርተኛም በአባልነት መርጣለች
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች (ዩኤኢ) በአረቡ ዓለም የመጀመሪያዋ ሴት የጠፈር ተመራማሪ ናት የተባለላትን የ27 ዓመቷን ኖራ አል ማትሮሺን የጠፈር ተመራማሪዎቿ አባል አድርጋ መረጠች፡፡
ዩኤኢ ሞሃመድ አል ሙላህ የተባለ ሌላ ጠፈርተኛንም በአባልነት መርጣለች፡፡
ሁለቱም የዩኤኢ ዜጎች ናቸው፡፡
አል ማትሮሺ እና አል ሙላህ የሃገሪቱን የጠፈር ተመራማሪዎች ቡድን ለመቀላቀል ካመለከቱ 4 ሺ አመልካቾች መካከል ተወዳድረው መመረጣቸውንም የሃገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዱባይ ገዢ ሼክ መሃመድ ቢን ረሺድ አል መክቱም አስታውቀዋል፡፡
አዲሶቹ ጠፈርተኞች ወደ ህዋ በመጓዝ የመጀመሪያው ከሆነው ሌላኛው ኤመራቲ ሃዛ አል ማንሱሪ እና ከተጠባባቂ ጠፈርተኛው ሱልጣን አል ኔያዲ ጋር ይሰራሉ ተብሏል፡፡
አል ማትሮሺ እና አል ሙላህ ለስራው ካመለከቱ 4,305 ኤመራቲዎች መካከል ነው የተመረጡት፡፡ ከአመልካቾቹ መካከል 1,400ው ሴት አመልካቾች ናቸው፡፡
ይህ በዘርፉ የሚስተዋለውን የጾታ ስብጥር ችግር ለመቅረፍ ሊያግዝ እንደሚችል ነው የተዘገበው፡፡
ችግሩን ለመቅረፍ በተለያዩ የዘርፉ ተቋማት ጥረቶች ተደርገዋል፤ አሁንም እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡
ሆኖም እስከተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ ድረስ ወደ ጠፈር ከተጓዙ 550 ተመራማሪዎች (አስትሮኖቶች) መካከል 65ቱ ብቻ ናቸው ሴቶች እንደ ዘ ናሽናል ዘገባ፡፡
የመሃመድ ቢን ረሺድ ጠፈር ምርምር ማዕከል ከአሜሪካው የጠፈር ምርምር ተቋም (ናሳ) ጋር 4 ጠፈርተኞችን ለማሰልጠን የሚያስችል ስምምነት በቅርቡ አድርጓል፡፡
በስምምነቱ መሰረትም አዲሶቹ ኤመራቲ ጠፈርተኞች ሂዩስተን ቴክሳስ በሚገኘው ጆንሰን ጠፈር ምርምር ማዕከል ሰልጥነው የኤመራቲ ባልደረቦቻቸውን የሚቀላቀሉ ይሆናል፡፡
ሃዛ አል ማንሱሪ እና ሱልጣን አል ኔያዲ በሩሲያ ነበር የሰለጠኑት፡፡
ዩኤኢ “ፕሮብ ሆፕ” የተሰኘችን መንኮራኩር በቅርቡ ማርስ ላይ በስኬት ለማሳረፍ መቻሏ የሚታወስ ነው፡፡