ኤምሬትስ ለአረቡ አለም የመጀመሪያ የሆነውን መንኮራኩር ወደ ማርስ አስወነጨፈች
ኤምሬትስ ለአረቡ አለም የመጀመሪያ የሆነውን መንኮራኩር ወደ ማርስ አስወነጨፈች
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለአረቡ አለም የመጀመሪያ የሆነውን የጠፈር መንኮራኩር ወደ ማርስ አስወንጭፋለች፤ይህም የሀገሪቱን የሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅም እንደሚያሳድግና በነዳጅ ላይ ያላትን ጥገኝነት እንደሚቀንስ ተገልጿል፡፡
የኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አንዋር ጋርጋሽ መንኮራኩር በማስወንጨፍ ታሪክ ተሰርቷል፤ በመሬትና በሰማይ መካከል ያለው እርቀትምያጥራል ብለዋል፡፡
“አል አማል” የተሰኘችው መንኮራኩሯ የተወነጨፈችው ተንጋሽማ ከተባለው የጃፓን የጠፈር ማእከል ሲሆን ወደ ጠፈር ደርሳ መረጃ ለመላክ የ7 ወር ጊዜ እንደሚፈጅባት ተነግሯል፡፡ ወደ ጠፈር የማስወንጨፍ ስራው ባለፈው ሳምንት ሊካሄድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም የአየር ጸባዩ ጥሩ ባለመሆኑ ሁለት ጊዜ ሊራዘም መቻሉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከተወነጨፈች ከአንድ ሰአት በኋላ መንኮራኩሯ ብርሃንን ወደ ኃይል ቀይራ መሬት ካለው የራዲዮ ኮሙኒኬሽን ጋር ግንኙነት መፍጠር እንደቻለችም ተገለጿል፡፡
አሁን ስምንት መንኮራኩሮች በማርስ ላይ እየተንቀሳቀሱ ሲሆን አንዳንዶቹ ፕላኔትን እየዞሩ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ አርፈውባታል፡፡ ቻይናና አሜሪካ እያንዳንዳቸው መንኮራኩር ለማስወንጨፍ አቅደዋል፡፡
የሳይንስ ሚኒስትር ሳራህ አሚሪ እንዳሉት ይችን መንኮራኩር ለማስወንጨፍ 200 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጭ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ የመንኮራኩሯ መወንጨፍ የማሪታንን አየርጸባይና፣ የእለታዊና የወቅታ ለውጦችን ሙሉ መረጃ መሰብሰብ አላማው መሆኑ ተዘግቧል፡፡
ኤምሬትስ መንኮራኩር ለመላክ አስባ የነበረው ከስድስት አመታት በፊት ነበር፡፡ ኤምሬትስ 9.4 ሚሊዮን ህዝብ ያላት መካከለኛው ምስራቅ የምትገኝ ሀገር ስትሆን ከዚህም ውስጥ አብዛኞቹ የውጭ ሀገር ዜጎች ናቸው፡፡
በፈረንጆቹ 2117 በማርስ ላይ ሰፈራ ለመጀመር አቅዳለች፡፡ ሀዛ አልመንሱር ባለፈው መስከረም ወር ወደ አለምአቀፍ የጠፈር ማእከል በመብረር የመጀመሪያው የኤምሬትስ ዜጋ መሆን ችሎ ነበር፡፡