የአረብ ሊግ ግድቡን በተመለከተ ያንጸባረቀው አቋም ምንድነው?
ሊጉ ባለፈው የካቲት ወር አካሂዶት በነበረው ስብሰባ ግብጽን የሚደግፍ ውሳኔ አሳልፎ ነበር
የአረብ ሊግ ኢትዮጵያ ግድቡን በተመለከተ “ብቸኛ እርምጃ” እንዳትወስድ ጥሪ አቀረበ
የአረብ ሊግ ኢትዮጵያ ግድቡን በተመለከተ “ብቸኛ እርምጃ” እንዳትወስድ ጥሪ አቀረበ
የአረብ ሊግ አባል ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ኢትዮጵያ ግድቡን በተመለከተ “ብቸኛ እርምጃ”ወይንም ያለስምምነት የውኃ ሙሌት እንዳትጀምር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ይህን ያሉት በትናንትናው እለት በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ስብሰባ ካደረጉ በኃላ ባወጡት የጋራ የአቋመ መግለጫ ነው፡፡
ሊጉ ባለፈው የካቲት ወር አካሂዶት በነበረው ስብስባ ግብጽ ያቀረበችውን ኢትዮጵያን የሚቃወምና ግብጽ በናይል ውሃ ላይ ያላትን “ታሪካዊ መብት” የሚገልጽን የውሳኔ ሀሳብ አጽድቆ ነበር፡፡ በጊዜው ሁሉም የሊጉ አባል ሀገራት የውሳኔ ሀሳቡን ሲደግፉ፣ሱዳን በግልጽ ተቃውማው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ በቅን መንፈስ ወደ ውይይቱ እንዲመለሱና ተጨማሪ ጥረት እንዲያደርጉ ሚኒስትሮቹ በአቋም መግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡
የድርድሩ መቋረጥ አሳስቦናል ያሉት ሚኒስትሮቹ ሶስቱም ሀገራት ከአመታት በፊት በካርቱም በፈረሙት የ“መርሆች ስምምነት” መሰረት አንዱ ሀገር በሌላኛው ላይ የጎላ ተጽእኖ በማያሳድርበት አግባብ ለስምምነቱ ተገዥ መሆን እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡
በስብሰባው ላይ ጅቡቲ፣ሶማሊያና ኳታር ግድቡን በሚመለከት የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ መቃወማቸውን የሚያሳዩ የተለያዩ ዘገባዎች ወጥተዋል፡፡
ግብጽ በቅርቡ ለተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በጻፈችው ደብዳቤ ግድቡ ለአለም አቀፍ ሰላምና ጸጥታ መደፍረስ ምክንያት እንዳይሆን ተመድ ጣልቃ መግባት እንደሚያስፈልገው ገልጻ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ግብጽ "በሀሰት የህዳሴው ግድብ ለአለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት ስጋት ነው" በማለት ለጸጥታው ምክር ቤት የላከችው ደብዳቤ ትክክል አይደለም የሚል ይዘት ያለው ደብዳቤ ለምክርቤት አስገብተዋል፡፡
ከግድቡ ጋር በተያያዘ “የሰላምና ጸጥታ መደፍረስ ቢያጋጥም በዛቻና ጠብ አጫሪ በሆነ ተግባር የተጠመደችው ግብጽ ኃላፊነቱን የምትወስድ” እንደምትሆን ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ግድቡ ለልማት የሚውል ፕሮጀክት መሆኑንና በታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት የጎላ ጉዳት እንደማያደርስ እየገለጸች ሲሆን በአንጻሩ ግብጽ ከናይል የምታገኘው የውሃ መጠን “ይቀንስብኛል” በማለት ቅሬታ ስታሰማ ቆይታለች፡፡
ግብጽና ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ የገቡ ሲሆን ሱዳን በአንጻሩ መሀል ላይ ለመሆን እየሞከረች ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ በድርድሩ ስምምነት ላይ ተደረሰም ፣ አልተደረሰ በመጪው ሀምሌ ወር የግድቡን የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት ከመጀመር እቅዷ ፈቅ እንደማትል እየገለጸች ነው፡፡ የኢትዮጵያን የውኃ ሙሌት እቅድ ግብጽና ሱዳን አይቀበሉትም፤ ስምምነት ላይ ሳይደረስ የዉኃ ሙሌት እቅድን አንቀበልም ብለዋል፡፡