የሰላም መደፍረስ ቢያጋጥም “ግብጽ ኃላፊነቱን ትወስዳለች”-ኢትዮጵያ
በቅርቡ ግብጽ የግድቡ ጉዳይ የአለም ሰላም ስጋት ስለሚሆን ተመድ ጣልቃ እንዲገባ ጠይቃ ነበር
የሶስትዮሽ ድርድር እየተካሄደ ባለበት ወቅት ግብጽ ተመድ ጣልቃ እንዲገባ መጠየቋ “ግራእንዳጋባት” ኢትዮጵያ ገለጸች
የሶስትዮሽ ድርድር እየተካሄደ ባለበት ወቅት ግብጽ ተመድ ጣልቃ እንዲገባ መጠየቋ “ግራእንዳጋባት” ኢትዮጵያ ገለጸች
ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ “የሰላምና ጸጥታ መደፍረስ ቢያጋጥም በዛቻና ጠብአጫሪ በሆነ ተግባር የተጠመደችው ግብጽ ኃላፊነቱን የምትወስድ” እንደምትሆን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡
ግብጽ በቅርቡ ለተመድ የጸጥታው ምክርቤት በጻፈችው ደብዳቤ ግድቡ ለአለምአቀፍ ሰላምና ጸጥታ መደፍረስ ምክንያት እንዳይሆን ተመድ ጣልቃ መግባት እንደሚያስፈልገው ገልጻ ነበር፡፡
ሚኒስትር ገዱ ግብጽ ”‘በሀሰት የህዳሴው ግድብ ለአለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት ስጋት ነው’ በማለት ለጸጥታው ምክርቤት የላከችው ደብዳቤ ትክክል ባለመሆኑ ይህን ደብዳቤ ለመጻፍ” መገደዳቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ እስካሁን በቅን መንፍስ እየተደራደረች ነው፤በዚህም ምክንያት መሻሻል መጥቷል ያሉት ሚኒስትሩ ነገርግን የግብጽ በቅኝ ገዥዎች ጊዜ የተፈረመውንና ኢትዮጵያ ያልሳተፈችበትን ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን መፈለግ ድርድሩ በፍጥነት እንዳይቋጭ ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡
አቶ ገዱ በጻፉት ደብዳቤ ግብጽ ኢትዮጵያ “ብቸኛ እርምጃ” ልትወስድ ነው የሚል ጫፍ የነካ ግብዝነት እያሳየች ነው፤”የብቻ እርምጃ በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ውስጥ የለም” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ በግድቡ ዙሪያ የሶስትዮሽ ድርድር እያካሄዱ ባለበት ወቅት ግብጽ ተመድ የጸጥታ ምክርቤት ጣልቃ እንዲገባ መጠየቋ ግራእንዳጋባቸው ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ምክርቤቱ “ግብጽ ሀቅን ኣዛብታ በቀረበችበት ደብዳቤ አይሳሳትም ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ያሉት ሚኒሰትሩ ግብጽ “በናይል ላይ ፍትሀዊ ያልሆነ የቅኝ ግዛት ጊዜ የነበረን ፍላጎት ለማረጋገጥ” የምታገርገውን ጥረት ተመድ ውድቅ እንዲያደርገው ጠይቃለች፡፡
ተመድ ስሶስቱ ሀገራት በግድቡ ዙሪያ በመካከላቸው ያለውን የጎላ ልዩነት እንዲፈቱ አሳስቧል፡፡ ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ ከአመታት በፊት በሱዳን ካርቱም በተፈራረሙት “የመርሆች ስምምነት” መሰረት ችግሩን እንዲፈቱ መክሯል፡፡
ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ግድቡ ለልማት የሚውል ፕሮጀክት መሆኑን በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት የጎላ ጉዳት እንደማያደርስ እየገለጸች ሲሆን በአንጻሩ ግብጽ ከናይል የምታገኘው የውሃ መጠን “ይቀንስብኛል” በማለት ቅሬታ ስታሰማ ቆይታለች፡፡
ግብጽና ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ የገቡ ሲሆን ሱዳን በአንጻሩ መሀል ላይ ለሞሆን እየሞከረች ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ በድርድሩ ስምምነት ላይ ተደረስም፣አልተደረስም በመጭው ሀምሌ ወር የግድቡን የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት ከመጀመር እቅዷ ፈቅ እንደማትል እየገለጸች ነው፡፡ የኢትዮጵያን የውኃ ሙሌት እቅድ ግብጽና ሱዳን አይቀበሉትም፤ ስምምነት ላይ ሳይደረስ የዉኃ ሙሌት እቅድን አንቀበልም ብለዋል፡፡