እንደአዲስ በተጀመረው የግድቡ ድርድር ላይ ግብጽ ምን አለች?
ኢትዮጵያ ድርድሩን በሚካፈሉት ታዛቢዎች ሚና ላይ ስምምነት አለመደረሱን ቀደም ብላ አስታውቃለች
ድርድሩ “ውጤታማ ነው ብሎ መግለጽ በጣም አስቸጋሪ” ነው ያለችው ግብጽ ኢትዮጵያ ያለስምምነት እርምጃ እንዳትወስድ ጠይቃለች
ድርድሩ “ውጤታማ ነው ብሎ መግለጽ በጣም አስቸጋሪ” ነው ያለችው ግብጽ ኢትዮጵያ ያለስምምነት እርምጃ እንዳትወስድ ጠይቃለች
የኢትዮጵያ፣የሱዳንና ግብጽ የውሃ ሚኒስትሮች በትናንትናው እለት ያካሄዱት ስብሰባ “ውጤታማ ነው ብሎ መግለጽ በጣም አስቸጋሪ” መሆኑን የግብጽ ውሃ ሀብትና መስኖ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያም በበኩሏ ሶስቱ ሀገራት “የታዛቢዎቹ ሚና ምን ይሁን ” በሚለው ጉዳይ ስምምነት ላይ አለመድረሳቸውን በውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴሯ በኩል ዛሬ ጠዋት በወጣው መግለጫ አስታውቃለች፡፡
የግብጽ ውሃ ሀብትና መስኖ ሚኒስቴር መግለጫ ስብሰባው ትኩረት ያደረገው ስለውይይት ሂደት፤ስለመወያያ ነጥቦችና ታዛቢዎች ስለሚኖራቸው ሚና ነበር፤ስለዚህ ዉጤታማ ነው ማለት እንደማይቻል አብራርቷል፡፡
እንደመግለጫው ከሆነ ኢትዮጵያ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ክርክር ከፍታለች፤ አዲስ ምክረ ሀሳብ አቅርባ እንዲታይላት መፈለጓና በዋሽንግተን ስምምነት ላይ የተደረሰባቸውን ጉዳዮች ላይም እየተከራከረች መሆኑን ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ በሀምሌ ወር ግድቡን ለመሙላት በያዘችው አቋም ላይም ጸንታለች ብሏል መግለጫው፡፡
ግብጽ፣ኢትዮጵያ ድርድሩ ሳያልቅና ስምምነት ላይ ሳይደረስ መሙላት እንደማትጀምር እንድታስታውቃት ግብጽ መጠየቋን መግለጫው ጠቅሷል፡፡
እንደመግለጫው በፈረንጆቹ የካቲት 2020 ሶስቱ ሀገራት ከተወያዩ በኋላ የአሜሪካና የአለም ባንክ በታዛቢነት ሲሳተፉ የአመቻችነት ሚና ነበራቸው፡፡
ግብጽ መግለጫው ድርድሩ የሚወስደው ጊዜም ከሰኔ 2 እስከ 6 ሲሆን በዚህ ጊዜ በግድቡ በሙሌትና አስተዳደር ላይ ሙሉ ስምምነት መደረስ አለበት የሚል አቋም አንጸባርቃለች፡፡
በትናንትነው እለት የተጀመረው ድርድር ደቡብ አፍሪካ፣የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ በታዛቢነት እየተሳተፉበት ይገኛሉ፡፡
በሶስቱ ሀገራት መካከል በአሜሪካ ሲካሄድ በነበረው ድርድር ላይ አሜሪካና የአለም ባንክ በታዛቢነት ቢሰየሙም፣ ወደማደራደርና ወደ ድርድር ሰነድ አርቃቂነት ሚናቸው ተቀይሯል በማለት ኢትዮጵያ ማለመስማማቷ ነበር ድርድሩ ሳይቋጭ የቀረው፡፡
ኢትዮጵያ ድርድሩ እንዲቀጥል ከተስማማች በኃላ የሶስቱ ሀገራት የውኃ ሚኒስትሮች ሴኔ 2 ቀን 2012 ዓ.ም በበይነ-መረብ ቪዲዮ ኮንፈረንስ እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው ልማትን ለማፋጠን መሆኑን በተደጋጋሚ ብትገልጽም በግብጽ በኩል ከናይል የማገኘው የውኃ መጠን ይቀንሳል የሚል ቅሬታ ሲነሳ ቆይቷል፡፡ሱዳን በአንጻሩ የግድቡን መገንባት እንደማትቃወም ስትገልጽ ቆይታለች፡፡
በመጭው ሀምሌ ወር የግድቡን ውሃ ሙሌት ለመጀመር ኢትዮጵያ እቅድ አውጥታ እየሰራች ሲሆን ሱዳንና ግብጽ ስምምነት ላይ ሳይረስ ሙሌቱ መጀመር የለበትም የሚል አቋም ይዘዋል፡፡