ሱዳን በህዳሴ ግድብ ላይ የዓረብ ሊግ ከግብፅ ጋር ለመቆም ያሳለፈውን የትብብር ውሳኔ ተቃወመች
ሱዳን በህዳሴ ግድብ ላይ የዓረብ ሊግ ከግብፅ ጋር ለመቆም ያሳለፈውን የትብብር ውሳኔ ተቃወመች
ትናንት የካቲት 25 ቀን 2012 ዓ.ም በግብጽ ካይሮ በተካሔደው የዓረብ ሊግ 153ኛ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ፣ የአረብ ሀገራት በግድቡ ዙሪያ ከግብጽ እና ሱዳን ጎን እንዲቆሙ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በ2015 የተደረሰውን የመርሆች መግለጫ ስምምነት በመጣስ የግድቡን ስራ በማከናወን ላይ እንደምትገኝ በመጥቀስ ክስ አቅርበዋል፡፡
ግብጽ ኢትዮጵያን በመወንጀል ለሊጉ ያቀረበችው ረቂቅ የድጋፍ ሰነድ፣ የዓረብ ሀገራት ኢትዮጵያን በመቃወም ከግብጽና ሱዳን ጋር እንዲቆሙ የሚጠይቅ ነው፡፡
የዓረብ ሊግም ግብጽ በናይል/አባይ ዉሀ ላይ ያላትን ታሪካዊ መብት የሚደግፍ እና የኢትዮጵያን የተናጥል ውሳኔ የሚኮንን ውሳኔ እንዳሳለፈ ተዘግቧል፡፡
ይሁንና ሰነዱ አይመለከተኝም ያለችው ካርቱም ከህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ሊጉ ከግብፅ እና ሱዳን ጋር እንዲቆም የሚጠይቀውን ረቂቅ የድጋፍ ሰነድ ውድቅ አድርጋለች፡፡ በግብጽ የቀረበው ሰነድ፣ ኢትዮጵያን የሚያስቀይም ከመሆኑም ባለፈ የሀገሯን ብሔራዊ ጥቅም እንደሚጋፋም ነው ሱዳን በስብሰባው ላይ ያነሳችው፡፡
ሱዳን እንደዚህ ያሉ ሰነዶች እና መግለጫዎች በግድቡ ዙሪያ የሚደረጉ ድርድሮችን ሊያደናቅፉ እና የዓረብ እና የኢትዮጵያን ግንኙነት የበለጠ ሊያበላሹ እንደሚችሉ አንስታ ተከራክራለች፡፡
የግብጽ የቀድሞ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የአሁኑ የዓረብ ሊግ ዋና ጸሀፊ አህመድ አቡል ጌቲ ሰነዱ ግብጽ በወንዙ ላይ ያላትን ታሪካዊ መብት የሚጥሱ ማናቸውንም ተግባራትን የሚቃወም እና ኢትዮጵያ በተናጠል የምትወስዳቸውን እርምጃዎች የሚጻረር እንደሆነ ለስብሰባው ታዳሚያን አብራርተዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ ፍትሀዊ እና የሶስቱንም ሀገራት ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው ያሉት በአሜሪካ የተዘጋጀው ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ተግባራዊ እንዲሆንም በግብጽ የተዘጋጀው ሰነድ ይጠይቃል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ ረቂቅ የስምምነት ሰነዱን እንድትፈርም የዓረብ ሀገራት አስፈላጊ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ሰነዱ እንደሚጠይቅም ነው አህመድ አቡል ጌቲ ያብራሩት፡፡
ይሁን እንጂ በግብጽ የተዘጋጀውን ሰነድ እንደማትቀበል በተወካይዋ በኩል የገለጸችው ሱዳን ከሰነዱ ስሟ እንዲወጣ አድርጋለች፡፡
ሚድል ኢስት ኒውስ እንደዘገበው የሱዳን አቋም በዓረብ ሊግ አባል ሀገራት ዘንድ አግራሞትን አጭሯል፡፡