የአረብ ሀገራት የፍልስጤማውያንን ከጋዛ ማስወጣት እንደሚቃወሙ ለአሜሪካ በጻፉት ደብዳቤ ገለጹ
ደብዳቤውን የጻፉት የጆርዳን፣ የግብጽ፣ የሳኡዲ አረቢያ፣ የኳታር እና የአረብ ኢምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የፍልስጤም ፕሬዝደንት አማካሪ ሁሴን አል ሼይክ ናቸው ተብሏል
ትራምፕ የእስራኤልና ሀማስ ጦርነት የፈራረሰችው ጋዛ እስከምትጸዳ ድረስ ግብጽና ጆርዳን በጋዛ የሚገኙ ፍልስጤማውያን እንዲያስጠልሏቸው ሀሳብ አቅርበው ነበር
የአረብ ሀገራት የፍልስጤማውያንን ከጋዛ ማስወጣት እንደሚቃወሙ ለአሜሪካ በጻፉት ደብዳቤ ገለጹ።
አምስት የአረብ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የፍልስጤም አስተዳደር ባለስልጣናት ለአሜሪካ በጻፉት ደብዳቤ ትራምፕ ባለፈው ወር ያቀረቡትን ፍልስጤማውያን ወደ ሌላ ሀገር የማዛወር ሀሳብ በመቃወም ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ደብዳቤ መጻፋቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ዘገባው እንደጠቀሰው ደብዳቤውን የጻፉት የጆርዳን፣ የግብጽ፣ የሳኡዲ አረቢያ፣ የኳታር እና የአረብ ኢምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የፍልስጤም ፕሬዝደንት አማካሪ ሁሴን አል ሼይክ ናቸው።
ትራምፕ 15 ወራት በዘለቀው የእስራኤልና ሀማስ ጦርነት የፈራረሰችው ጋዛ እስከምትጸዳ ድረስ ግብጽና ጆርዳን በጋዛ የሚገኙ ፍልስጤማውያን እንዲያስጠልሏቸው ሀሳብ አቅርበው ነበር።
ፕሬዝደንት ለአጭር ወይም ለረጅም ጊዜ እንደሆነ ሲጠየቁ "ከሁለት አንዱ" የሚል መልስ ነበር የሰጡት። ትራምፕ የሰጡት አስተያየት ከቀያቸው እንደሚፈናቀሉ ለረጅም ጊዜ ሲሰጉ የነበሩትን ፍልስጤማውያን ስጋት አስተጋብቷል። ጆርዳን፣ ግብጽና ሌሎች የአረብ ሀገራት ይህን እቅድ በጽኑ ተቃውመውታል።
"በጋዛ የሚከናወነው መልሶ ግንባታ በጋዛ ህዝብ ቀጥተኛ ተሳትሮ መሆን አለበት። ፍልስጤማውያን በመሬታቸው እየኖሩ በመልሶ ግንባታው መሳተፍ አለባቸው" ብሏል ደብዳቤው።
ሀገራቱ ፍልጤማውያን በመልሶ ግንባታ ሂደቱ ባለቤት ሊሆኑ ይገባል ሲሉ በደብዳቤው ጠቅሰዋል።
የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው መጠነሰፊ ጥቃት ከ47ሺ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል። እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት የዘር ማጥፋት ክስ አስተባብላለች።
ሀማስ ጥቅምት 7፣2023 በደቡብ እስራኤል ድንበር ጥሶ በመግባት 1200 ሰዎችን ከደገለ እና 250 ሰዎችን አግቶ መወሰዱን ተከትሎ ነበር ሀሰማስና እስራኤል ወደ አጠቃላይ ጦርነት የጠቡት።