ዲ.አር ኮንጎ አርሰናልን ጨምሮ የአውሮፓ ክለቦች ከሩዋንዳ ጋር ያለቸውን የስፖንሰር ስምምነት እንዲያቋርጡ ጠየቀች
ኮንጎ ለአርሰናል፣ ፒኤስጂና ባይርሙኒክ ክለቦች በጻፈችው ደብዳቤ ከሩዋንዳ “የደም ገንዘብ ከመቀበል ተቆጠቡ” ብላለቸ
የሩዋንዳ መንግስት ለኮንጎ አማጽያን በሚያደርገው ድጋፍ ነው ስምምነቱ እንዲቋረጥ መንግስት ጥያቄውን ያቀረበው
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አርሰናል፣ ባየር ሙኒክ እና ፓሪስ ሴንት ዠርሜይን ከ”ቪዚት ሩዋንዳ” ጋር ያደረጉትን የስፖንሰርሺፕ ስምምነት እንዲያቋርጡ ጠይቃለች።
ጥሪው የቀረበው በሩዋንዳ መንግስት ይደገፋሉ የሚባሉት የኤም 23 አማፂያን በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ትልቋን ከተማ ጎማን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ ባወጣው ሪፖርት በአማጺያኑ እና በመንግስት ሀይሎች መካከል በሚደረገው ጦርነት በዚህ አመት ብቻ ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡
ተመድ አክሎም የሩዋንዳ መንግስት የኤም 23 አማጽያንን ወታደራዊ ዘመቻ እንደሚመራ ፣ እንደሚያስታጥቅ እና እንደሚደግፍ ይከሳል፡፡
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴሬስ ካይክዋምባ ዋግነር ለአርሰናል እና ፒኤስጂ ባለቤቶች እና ለባየር ሙኒክ ፕሬዝዳንት ኸርበርት ሃይነር በጻፍነው ደብዳቤ ስለ ስምምነቱ “ሞራላዊ ተገቢነት” እንዲጠይቁ አሳስበናል ብለዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ የ”ቪዚት ሩዋንዳ” ስፖንሰር ወጪ የሚሸፈነው በአማጽያን ቁጥጥር ስር ከሚገኙ የማአድን ስፍራዎች የሚወጡ ማዕድኖች ወደ ሩዋንዳ ተጓጉዘው ለአለም አቀፍ ገበያ ከቀረቡ በኋላ በሚገኝ ገንዘብ ነው ሲሉ ወንጅለዋል፡፡
"ለአርሰናል በተጻፈው ደብዳቤ “አርሰናል ይህን በደም የተጨማለቀ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት የሚያቋርጠበት ጊዜው አሁን ነው” ሲሉ ማሳሰባቸው ተነግሯል
ደብዳቤው “ክለቦቹ ለህሊናቸው ካልሆነም በሩዋንዳ ድጋፍ በአማጽያን ጥቃት ኢላማ ለሆኑ ዜጎች ሲሉ ከሩዋንዳ ጋር ስምምነታቸውን እንዲያቋርጡ” ጥሪ ማቅረቡን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር በአለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተጽዕኖ ለማጉላት “ቪዚት ሩዋንዳ” በሚል መሪ ቃል የተለያዩ የአውሮፓ እግር ኳስ ቡድኖችን ስፖንሰር ታደርጋለች፡፡
ከሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል ጋር ይህን የስፖንሰር ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ የጀመረችው ከ2018 አንስቶ ሲሆን በቅርቡ የተደረሰው ስምምነት ማሻሻያ ኪጋሊ ለመድፈኞቹ በአመት 12.39 ሚሊየን ዶላር የስፖንሰር ክፍያ እንደምትከፍል ያስቀምጣል፡፡
ሀገሪቱ በ2019 ከፒኤስጂ ጋር ተመሳሳይ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ላይ ደርሳለች ፤ የጀርመኑ ባየር ሙኒክ በበኩሉ በ2023 ከሩዋንዳ ጋር የአምስት አመት የእግር ኳስ ልማት እና ቱሪዝም ማስተዋወቅ አጋርነት ተፈራርሟል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሚ የ”ፎርሙላ 1” አለም አቀፍ የመኪና ውድድርን ለማዘጋጀት ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡