ሳዑዲን ጨምሮ 4 የአረብ ሃገራት በግድቡ ጉዳይ ግብጽን ደግፈው መግለጫ አወጡ
ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ትናንት “ከግብጽ የውሃ ድርሻ ላይ ማንም አንዲትንም ጠብታ ሊነካ” እንደማይችል የሚያሳስብ ንግግር ማድረጋቸው የሚታወስ ነው
ሃገራቱ “የግብጽ የውሃ ደህንነት ጉዳይ የመላው አረብ ብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው” ብለዋል በመግለጫቸው
ሳዑዲን ጨምሮ 4 የተለያዩ የአረብ ሃገራት በግድቡ ጉዳይ ግብጽን ደግፈው መግለጫ አወጡ፡፡
ሃገራቱ ከግብጽ እና ሱዳን ብሔራዊ እና የውሃ ደህንነት መጠበቅ እንዲሁም ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ያላቸውን አጋርነት አሳውቀዋል፡፡
የታችኞቹን የናይል ተፋሰስ ሃገራት ደግፋ መግለጫ ያወጣችው ሳዑዲ “የግብጽ የውሃ ደህንነት ጉዳይ የመላው አረብ ብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው” ብላለች፡፡
የሃገሪቱ ዜና አገልግሎት ዛሬ ጠዋት ይዞት በወጣው በዚህ መግለጫ ሪያድ “የግድቡ ጉዳይ የሁሉንም ፍላጎት ባሳካ መልኩ መቋጫ እንዲያገኝ ለማድረግ”ለሚደረጉ ጥረቶች ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቃለች፡፡
ሳዑዲ በዓለም አቀፍ ህግጋትና መርሆዎች መሰረት “አሳሪ” ከሆነ ስምምነት (binding agreement) በቶሎ ለመድረስ ድርድሩን በጥሩ የመተማመን መንፈስ መቀጠል እንደሚገባ ነው ያሳሰበችው፡፡
የኦማን ሱልጣኔትም “ግብጽ የግድቡን ጉዳይ በውይይትና ድርድር ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት” እንደምትደግፍ ገልጿል፡፡
የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “አለኝ” የሚለውን አጋርነት በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫው በመደረግ ላይ ያለው ጥረት “በቀጠናው መረጋጋትን ሊያመጣ እና የሁሉንም ወገኖች ጥቅም ሊያስጠብቅ የሚችል” ነው ብሏል፡፡
የመንም ከግብጽ ጎን መቆሟን በመጠቆም የአጋርነት መግለጫን አውጥታለች፡፡
የመን ግብጽ “በግድቡ ጉዳይ ፍትሐዊ መፍትሄን ለማፈላለግ ብቻም ሳይሆን ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት” ታደርጋለች ያለችውን ያላሰለሰ “ጥረት” ጭምር ነው እንደምትደግፍ ያስታወቀችው፡፡
የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “የግብጽ የውሃ ደህንነት ጉዳይ የመላው አረብ ብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው” ብሏል በመግለጫው፡፡
ሚኒስቴሩ በመግለጫው የተፋሰሱን ሃገራት ጥቅም የሚጎዳ ምንም ዓይነት የተናጠል እርምጃ መውሰድ እንደማያስፈልግ ነው ያሳሰበው፡፡
ባህሬይንም የህዝቦቿን ፍላጎት እና የመኖር መብት ለመጠበቅ ነው እያደረገችው ያለው በሚል ከግብጽ ጎን መቆሟን አሳውቃለች፡፡
የግድቡ የሙሌት እና የትግበራ ጉዳይ የተፋሰሱን ሃገራት ጥቅም ባስጠበቀ እና ዓለም አቀፍ ህግጋትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እልባት እንዲያገኝ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶችን እንደምትደግፍም የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ትናንት ማክሰኞ በስዊዝ ቦይ ጉብኝት ያደረጉት የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ በስፍራው ተገኝተው ለነበሩ ብዙሃን መገናኛዎች ዛቻ አከል መግለጫን ሰጥተዋል፡፡
“ከግብጽ ውሃ ማንም አንዲትንም ጠብታ ሊነካ አይችልም” ሲሉ የተናገሩት ሲሲ “ይህ ከሆነ ግን ማንም ሊያስበው የማይችል አለመረጋጋት በቀጣናው (ምስራቅ አፍሪካ) ይፈጠራል” ሲሉ ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው፡፡
የግብጽ የውሃ ድርሻ ማንም ሊነካው የማይችል “ቀይ መስመር” እንደሆነ አድርገውም ነበር ሲሲ ሲያሳስቡ የነበሩት፡፡
በታላቁ የአባይ ወንዝ ላይ ታላቁን የህዳሴ ግድብ በመገንባት ላይ ያለችው ኢትዮጵያ ጉዳዩን በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በድርድር ለመፍታት ያላትን ዝግጁነት ደጋግማ መግለጿ አይዘነጋም፡፡