ሱዳን ከኢትዮጵየ ጋር በሕዳሴው ግድብና በድንበር ጉዳይ በዩኤኢ የቀረበላትን የ ላደራድራችሁ ጥያቄ መቀበሏን ገለጸች
በተለይ ከድንበር ጋር በተያያዘ የሱዳን እና ኢትዮጵያ አለመግባባት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አይሏል
የዩኤኢን ጥያቄ እና ጥያቄውን ሱዳን መቀበሏን በዜና መልክ መስማታቸውን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሕዳሴው ግድብና በድንበር ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር ላደራድራችሁ በሚል ያቀረበችውን ጥያቄ ሱዳን መቀበሏን የሀገሪቱ መንግስት ቃል አቀባይ ሀምዛ ባሉል ተናግረዋል፡፡
የሀገሪቱ የሽግግር ካቢኔ ስብሰባ ተቀምጦ በዩኤኢ ጥያቄ ላይ ከመከረ በኋላ ውሳኔ ማሳለፉን ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሱዳንን ከኢትዮጵያ ጋር በድንበሩ ጉዳይ እና በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ላደራድርሽ የሚል ጥያቄ ማቅረቧን እና ሱዳን ጥያቄውን መቀበሏን በዜና መልክ መስማታቸውን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለሱዳን ያቀረበችውን የላደራድራችሁ ጥያቄ ለኢትዮጵያ ስለማቅረቧ ላነሳንላቸው ጥያቄ ፣ “በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃ የለኝም ፤ በቀጣይ ይፋ እናደርጋለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል ከሕወሓት ኃይል ጋር ወደ ውጊያ መግባቷን ተከትሎ ሱዳን አወዛጋቢውን የ “አል ፋሻቃ” አካባቢ ጦሯ መቆጣጠሩን ገልጻለች፡፡ ሱዳን ቦታው በኢትዮጵያ ተይዞ የቆየ የግዛቷ አካል መሆኑን ስትገልጽም ሰንብታለች፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ በበኩሏ በሱዳን ወረራ እንደተፈጸመባት ይፋ አድርጋለች፡፡ ኢትዮጵያ በድንበር ጉዳይ ከሱዳን ጋር ለድርድር የምትቀመጠው የሱዳን ጦር በቅርቡ የያዛቸውን አካባቢዎች ለቆ ከወጣ ብቻ እንደሆነም መግለጿ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ እና ሱዳን የድንበር ውዝግብ የቆየ ቢሆንም ፣ በትግራይ ክልል ውጊያ ከተጀመረ ከቀናት በኋላ ሱዳን ይገባኛል የምትለውን ቦታ በኃይል መቆጣጠሯን ተከትሎ ውዝግቡ አይሏል፡፡ ሁለቱ ሀገራት ከድንበር ጉዳይ ጋር በተያያዘ እርስ በርስ በመወነጃጀል በተደጋጋሚ መግለጫዎችን አውጥተዋል፡፡
ሌላው በሁለቱ ሀገራት መካከል ልዩነት ያለበት ጉዳይ ፣ ግብፅንም የሚያካትተው የሕዳሴው ግድብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ፣ ሱዳን እና ግብፅ ላለፉት 10 ዓመታት በግድቡ ጉዳይ ላይ በመደራደር ላይ ቢሆኑም ድርድሩ ዛሬም አልተቋጨም።
ከአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪ ተመድ ፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት ሦስቱን ሀገራት እንዲያደራድሩ በቅርቡ ሱዳን ሀሳብ ማቅረቧም ይታወቃል፡፡ ይህ ሀሳብ በግብፅ ከመደገፉም ባለፈ ሁለቱ ሀገራት የጋራ ስጋት አለብን በሚል ወታደራዊ የትብብር ስምምነትም ተፈራርመዋል፡፡ ኢትዮጵያ በበኩሏ ከአፍሪካ ሕብረት ውጭ አደራዳሪ እንዳማትሻ አስታውቃለች፡፡