መራዘሙ በቂ ውሃ ለመያዝና መረጃ ለመለዋወጥ እንደሚያግዛት ካርቱም ገልጻለች
ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን ውሀ መሙያ ጊዜ ወደ መስከረም እንድታራዝም ሱዳን ጠየቀች።
የሱዳን ነዳጅ እና ሀይል ሚኒስትር ጃዲን ኦቤድ በሱዳን የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ እና ከአውሮፓ ህብረት ልኡክ ሮበርት ቫንዶል ጋር በካርቱም ተወያይተዋል።
ሚኒስትሩ ለአምባሳደሮቹ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ውሀ ሙሌት የሶሰትዮሽ ስምምነት ሳይደረግ ሀምሌ ወር ላይ መሙላት ብትጀምር በሱዳን ያለውን የኤሌክትሪክ እጥረት ያባብሰዋል ብለዋል።
በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ በመጭው ሀምሌ ወር ላይ የያዘችውን የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ወደ መስከረም እንድታራዝም ሱዳን ጠይቃለች።
የግድቡ ውሃ መሙያ ጊዜ ወደ መስከረም መራዘሙ ሱዳን እና ግብጽ አስቀድመው በቂ ውሃ እንዲይዙ ከማድረጉ በተጨማሪ ስለግድቡ በቂ መረጃ ለመለዋወጥ ያስችላል ሲሉ ሚኒስትሩ አክለዋል።
በሱዳን የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ሱዳን እና ግብጽ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ወደ ስምምነት እንዲመጡ የአሜሪካ ፍላጎት መሆኑን ገልጸው ይህ እንዲሆን አገራቸው ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረዋል።