የአርጀንቲናው የዓለም ዋንጫ አሸናፊ አሰልጣኝ ሞነቲ ህይወቱ አለፈ
ሞነቲ ከ1982ቱ የዓለም ዋንጫ በኋላ ብሔራዊ ቡድኑን ለቆ ወደ ባርሴሎና ክለብ በማቅናት በ1983 በኮፓ ዴል ሬይ ስኬት እንዲያስመዘግብ አስችሎታል
የአርጀንቲና ፕሬዝደንት ጃቪየር ሜሊ "ለሀገሪቱ ትልቅ ደስታ አምጥቶ የነበረው የቡድን መሪ በመለየቱ ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶናል" ብለዋል
የአርጀንቲናው የዓለም ዋንጫ አሸናፊ አሰልጣኝ ሞነቲ ህይወቱ አለፈ።
አርጀንቲና የ1978ቱን የአለም ዋንጫ እንድታነሳ ያስቻሏት አሰልጣኝ ሉይስ ሞነቲ በ85 አመቱ ህይወቱ ማለፉን የአርጀንቲና እግር ኳስ ፌደሬሽን በትናንትናው እለት አስታውቋል።
ለሮዛሪዎ ሴንትራል፣ ለቦካ ጁኒየርስ እና ሳንቶስ የተጫወተው ሞነቲ በ1974 የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ከመሆኑ በፊት የአሰልጣኝነት ዘመኑን በኒውዌል ኦልድ ቦይስ ጀምሮ በ1973 ከሁራካን ጋር የአርጀንቲናን ሻምፒዮንስሺፕ ውድድር ማሸነፍ ችሎ ነበር።
"የአርጀንቲና እግር ኳስ ፌደሬሽን በአሁኑ ወቅት የብሔራዊ ቡድኖች ዳሬክተር እና የቀድሞው የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ሴዛር ሉይስ ሞነቲን ስናሳውቅ በታላቅ ሀዘን ውስጥ ሆነን ነው። በሰላም አረፍ፣ፍላኮ ኩይርዶ" ብሏል ፌደሬሽኑ ባወጣው መግለጫ።
ሞነቲ ከ1982ቱ የዓለም ዋንጫ በኋላ ብሔራዊ ቡድኑን ለቆ ወደ ባርሴሎና በማቅናት ክለቡ በ1983 በኮፓ ዴል ሬይ ስኬት እንዲያስመዘግብ አስችሎታል።
የአርጀንቲና የ2022 የኳታር የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ሊዮነል ሜሲ በማህበራዊ ገጹ "ከእግር ኳስ ምልክቶቻችን አንዱ የሆነው ጥሎን ሄዷል። ለቤተሰቦቹ እና ጓደኞቹ መጽናናትን ይስጣቸው፤ ነፍሱን ይማር" ብሏል።
ሞነቲ በስፔን፣ በጣሊያን እና በሜክሲኮ ክለቦች ተጽዕኖ ነበረው።
የአርጀንቲና ፕሬዝደንት ጃቪየር ሜሊ በኤክስ ገጻቸው "ለሀገሪቱ ትልቅ ደስታ አምጥቶ የነበረው የቡድን መሪ በመለየቱ ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶናል" ብለዋል።
የአርጀንቲና እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝደንት ክላውዲዮ ታፒያም ሞነቲ እግር ኳስ ለሚያፈቅሩ ሁሉ የማይሞት ማስታዎሻ ጥሎ አልፏል ሲሉ ተናግረዋል።