ሜሲ በሆንግ ኮንግ አለመሰለፉ አድናቂዎቹን አስቆጣ
አርጀንቲናዊው ኮከብ ኢንተር ሚያሚ በሆንግ ኮንግ ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ አልተሰለፈም፤ በስታዲየም በመዘዋወር ለአድናቂዎቹ ሰላምታ አልሰጠም
ከወትሮው ከአምስት እጥፍ በላይ ከፍለው ስታዲየም የተገኙ ደጋፊዎችም “ዴቪድ ቤካም ገንዘባችን ይመልስ” በሚል ተቃውሟቸውን አሰምተዋል
የአሜሪካው ኢንተርሚያሚ በትናንትናው እለት ከቻይናው ሆንግ ኮንግ 11 ክለብ ጋር የወዳጅነት ጨዋታውን አድርጓል።
በሆንግ ኮንግ ደማቅ አቀባበል የተደረገለት አርጀንቲናዊው አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ በጨዋታው ላይ እንደሚሰለፍ መነገሩን ተከትሎም በርካታ አድናቂዎቹ ስታዲየም ለመግባት በውድ ትኬት ገዝተዋል።
ኢንተር ሚያሚ 4 ለ 1 ባሸነፈበት ጨዋታ ግን የጡንቻ ጉዳት ገጥሞታል የተባለው የ36 አመቱ አጥቂ አልተሰለፈም።
ጨዋታው እንደተጠናቀቀም ሜሲን ለመመልከት 1 ሺህ የሆንግ ኮንግ ዶላር (125 ዶላር) የከፈሉ አድናቂዎቹ የኢንተር ሚያሚ ባለቤት ዴቪድ ቤካም “ገንዘባችን ይመልስልን” የሚል ድምጻቸውን ማሰማታቸውን ስካይ ኒውስ አስነብቧል።
የሆንግ ኮንግ መንግስትም የወዳጅነት ጨዋታውን ያዘጋጀው ታትለር ኤሽያ ሜሲ ቢያንስ በሁለተኛው አጋማሽ ለ45 ደቂቃዎች እንደሚጫወት ማረጋገጫ ማግኘቱን ቢገልጽም አርጀንቲናዊው ኮከብ ወደ ሜዳ አለመግባቱ ቅሬታ ማስነሳቱን ጠቅሷል።
የስምንት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው በጨዋታው ላይ ባይሰለፍም በስታዲየም ለተገኙት አድናቂዎቹ እየተዘዋወረ ደስታቸውን እንዲጋራ ለማድረግ ቢታሰብም ሳይሳካ መቅረቱ ነው የተገለጸው።
ይህም አድናቂዎቹን እና የሆንግ ኮንግ ስፖርት አመራሮችን አስቆጥቷል።
ዴቪድ ቤካም በስታዲየም ለደጋፊዎች መልዕክት ለማስተላለፍ ሲሞክርም በርካታ ደጋፊዎች በጩኸት ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ታይቷል።
ለዚህም የወዳጅነት ጨዋታው አዘጋጁ አካል ሃላፊነቱን ይወስዳል ያለው የሆንግ ኮንግ ባህል፣ ስፖርትና ቱሪዝም ቢሮ፥ የትኬት ዋጋው ላይ ቅናሽ ተደርጎ ለተመልካቾቹ እንዲመለስ አሳስቧል።
ባለፈው ሳምንት ከሳኡዲው ክለብ አል ናስር ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደረገው ኢንተር ሚያሚ ሮናልዶ ሳይሰለፍ የ6 ለ 1 ሽንፈት ማስተናገዱ ይታወሳል።