ሜሲ ጫማ ከሰቀለ በኋላ “10” ቁጥር መለያው ጥቅም ላይ እንዳይውል አርጀንቲን ወስናለች
አርጀንቲና ዲያጎ ማራዶናን ለማክበር ተመሳሳይ ውሳኔ ብታሳልፍም በፊፋ ውድቅ መደረጉ ይታወሳል
ሊዮኔል ሜሲ ለነጭና ሰማያዊ ለባሾቹ 180 ጨዋታዎችን አድርጎ 106 ጎሎችን አስቆጥሯል
አርጀንቲና ተወዳጅ ተጫዋቿን ሊዮኔል ሜሲ ለማክበር ሲጠበቅ የነበረ ውሳኔ ማሳለፏ ተነግሯል።
የሀገሪቱ እግርኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት ካልውዲዮ ታፒያ ለስፔኑ አስ ጋዜጣ እንደተናገሩት፥ ሜሲ ከአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን መለያየቱን ሲያሳውቅ የሚለብሰው መለያ ቁጥር “10” አብሮ ይሰናበታል።
“ሜሲ ለብሄራዊ ቡድኑ መጫወት ሲያቆም የትኛውም ተጫዋች ታሪካዊውን የሜሲ የመለያ ቁጥር (10) ለብሶ እንዲጫወት አንፈቅድም” ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ።
የመለያ ቁጥሩ ሜሲን ለማክበር ሲባል ከብሄራዊ ቡድኑ የመለያ ቁጥሮች ዝርዝር ውጭ እንደሚደረግም በማከል።
ክለቦች ልዩ ክብር ለሚገባቸው ተጫዋቾቻቸው መሰል ውሳኔ ሲያሳልፉ ቢታይም በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ግን የተለመደ አይደለም።
አርጀንቲና የአለማችን የእግርኳስ ፈርጡን ዲያጎ ማራዶና ለማክበር ጨዋታ ሲያቆም የነገሰበትን የመለያ ቁጥር (10) ሌሎች ተጫዋቾች እንዳይለብሱት ብትወስንም የአለም የእግርኳስ ማህበር (ፊፋ) ውሳኔዋን ውድቅ እንዳደረገባት ይታወሳል።
ከማራዶና ተመሳሳይ የመለያ ቁጥር ለብሶ ሀገሩን ሻምፒዮን ያደረገውን ሜሲ ታሪካዊ የመለያ ቁጥር ሌሎች አርጀንቲናውያን ኮከቦች እንዳይለብሱት በተላለፈው ውሳኔ የፊፋ ምላሽ ይጠበቃል።
በፈረንጆቹ 2005 ለአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን መሰለፍ የጀመረው ሊዮኔል ሜሲ በ180 ጨዋታዎች 106 ጎሎችን አስቆጥሯል፤ 53 ጎል የሆኑ ኳሶችን አቀብሏል።
ሜሲ ሀገሩን ከ36 አመት በኋላ በ2022ቱ የኳታር የአለም ዋንጫ ሻምፒዮን ማድረጉን ተከትሎ ከብሄራዊ ቡድኑ ይሰናበታል የሚሉ መረጃዎች ሲወጡ መቆየታቸው ይታወሳል።
የስምንት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው በባርሴሎና እና ፓሪስ ሴንት ጀርሜን የተሳካ ቆይታ ነበረው።
ሜሲ 10 ቁጥር ማልያውን ለብሶ ከባርሴሎና ጋር 34 (10 ላሊጋ፣ ሰባት ኮፓዴላሬ እና አራት የሻምፒዮንስ ሊግ) ዋንጫዎችን አንስቷል።
ለፈረንሳዩ ፒኤስጂም በ74 ጨዋታዎች 32 ጎሎች ማስቆጠሩና ሶስት ዋንጫዎችን ከክለቡ ጋር ማንሳቱ የሚታወስ ነው።
አርጀንቲናዊው ኮከብ ወደ አሜሪካው ኢንተርሚያሚ ከተዛወረ በኋላም ስኬት አልራቀውም።