የኳስ ፍቅር የህዝብ አውቶብስ ያስጠለፈው አርጀንቲናዊ መጨረሻው እስር ቤት ሆኗል
የአርጀንቲናና ከክሮሽያ ጨዋታን ለመመልከት የቋመጠው ግለሰቡ ጀቆመ የአውቶብስ አስነስቶ በፍጥነት ለመንዳት ሞክሯል
ግለሰቡ በፖሊስ ክትትል በመያዙ የጓጓለትን ጨዋታ ሳይመለከት ለእስር ተዳርጓል
የነዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ሃገር በእግር ኳስ ፍቅር የነደዱ እልፍ ሰዎች መገኛ ናት።
ከሰሞኑ አርጀንቲና በኳታር ከክሮሽያ ጋር ስትጫወት ቦነሳይረስን ጨምሮ በርካታ የአርጀንቲና ከተሞች ልዩ ድባብ ነበራቸው።
ይህን ጨዋታ አለመመልከት በህይወት ምዕራፍ ውስጥ ትልቁን ቦታ እንደመነጠቅ የተመለከቱት አርጀንቲናውያን ስራ ያለው ከስራው ቀርቶ ቴሌቪዥን ከፍቶ ይጠባበቃል።
የ53 አመቱ ጎልማሳ ግን ይህ እድል የሚያመልጠው መስሎ ተሰምቶታል።
በቦነሳይረስ መሃል ከተማ ሲዩዳድ ሳንታ ማሪያ አካባቢ ነዋሪ የሆነው የኳስ አፍቃሪ እየተጓዘበት ያለው የህዝብ ትራንስፖርት የሚሰጥ አውቶብስ አካሄድ ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ቤቱ እንደማያደርሰውም አምኗል።
እናም ቀይ መብራት በርቶ አውቶብሱ ሲቆምና ሾፌሩም እቃ ለመሸመት ወደ ሱቅ ባመራበት ቅጽበት አንድ ሃስብ ወደ አዕምሮው ይመጣል፤ መሪውን ጨብጦ ወደ ፊት መገስገስ።
ያሰበውንም አደረገው፤ በመንገደኞች የተሞላውን አውቶብስ በፍጥነት ወደ ቤቱ መንዳት ጀመረ።
ባሰበው ፍጥነት ደርሶ ግን ጨዋታውን መመልከት አልቻለም።
በሁኔታው የተደናገጠው ሾፌር ለፖሊስ በማሳወቁ የትራፊክ ፖሊሶች ከበፊትና ኋላ ተከታትለው አስቆሙት።
ግለሰቡ ከ6 ኪሎሜትሮች በላይ አሽከርክሮ አውቶብሱን አቁሞ ሮጦ ለማምለጥ ቢሞክርም በመኖሪያ ቤቱ አቅራቢያ በቁጥጥር ስር ውሏል።
የአርጀንቲና መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ጎልማሳው ለእግር ኳስ ፍቅሩ የከፈለው ዋጋ ጨዋታውን ከጅማሮው ማየት አይደለም ከነጭራሹ እንዲከታተል አላስቻለውም።
በፖሊስ በቁጥጥር ስር ውሎም የህዝብ ትራንስፖርትን በማወክና አውቶብስ ጠልፎ በማምለጥ ክስ ምርመራ እየተደረገበት ነው።
ስሙ ያልተጠቀሰው ግለሰብ አዳሩን በፖሊስ ጣቢያ ቢያደርግም ሀገሩ ክሮሽያን 3 ለ 0 በመርታት ለፍጻሜው ማለፏን በማወቁ ደስተኛ ሆኗል።
የፊታችን እሁድ ከፈረንሳይ ጋር የምታደርገውን ጨዋታስ በቤቱ ሆኖ ይመለከታል? ወይስ በማረሚያ ቤት? የሚለው ግን አልታወቀም።
የሜሲ ሀገር የ53 አመቱን ጎልማሳ የኳስ ፍቅር በመረዳት በማስጠንቀቂያ ለቃው ፍጻሜውን ይመለከት ዘንድ የበርካታ የስፖርት ወዳጆች አስተያየት ነው።
የእግር ኳስ አፍቃሪዎች በተለይ የአለም ዋንጫ ጨዋታዎች ሲደረጉ የሚከውኗቸው አስደናቂ ነገሮች የመገናኛ ብዙሃንን ቀልብ ስበው መነጋገሪያ ሲሆኑ ይታያል።
በቻይና ለሰባት ተከታታይ ቀናት እንቅልፉን መስዋዕት እያደረግ የአለም ዋንጫ ጨዋታዎችን የተመለከተ ወጣት ፊቱ ፓራላይዝ መሆኑ በቅርቡ መዘገቡ ይታወሳል።