ሳዑዲ አረቢያ ሳትጠበቅ አርጀንቲናን አሸንፋለች
በአለም ዋንጫው 18 ጊዜ ተሳትፋ 2 ዋንጫ ያነሳችው አርጀንቲና ፤ የስድስት ጊዜ ተሳትፎ ባላት ሳኡዲ አረቢያ ነው የተሸነፈችው
የሊዮኔል ሜሲ ሃገር ለጥሎ ማለፉ ቅድሚያ ቢሰጠውም በሳዑዲ አረቢያ 2ለ1 ተሸንፏል
በአለም ዋንጫው ሳኡዲ አረቢያ የዋንጫ ተጠባቂዋን አርጀንቲናን ድል አደረገች።
ሰባት ጊዜ ባሎንዶር የወሰደው ሜሲ በ10 ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት ጎል አርጀንቲናን ቀዳሚ ሲያደርግ የውሃ ሰማያዊ ለባሾቹ ድል አይቀሬ መስሎ ነበር።
የአል ሂላሎቹ ሳሌም ዳውሳሪ እና ሳሌህ አል ሸህሪ ያስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች ግን አረንጓዴ ወፎቹን አስደሳች ድል አጎናፅፈዋል።
የአለም ዋንጫውን ያሰናዳችው ኳታር በየብስ የምትዋሰነው ከሳኡዲ ብቻ እንደመሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ የሳኡዲ ደጋፊዎች የሉሳይል ስታዲየምን አድምቀውታል።
ከ88 ሺህ በላይ ተመልካቾች በስታዲየም የተመለከቱት ጨዋታ በአለም ዋንጫ ያልተጠበቀ ውጤት ከተመዘገበባቸው ጨዋታዎች መካከል የሚመዘገብ ይሆናል።
በ2018ቱ የአለም ዋንጫ በመክፈቻው በሩስያ የ5 ለ 0 ሽንፈት የገጠመው የሳኡዲ አረቢያ ብሄራዊ ቡድን ነው በኳታር አርጀንቲናን ያሸነፈበት ያሸነፈው።
በ1994 የአለም ዋንጫ 16 ውስጥ የገባችበት ውጤት የተሻለ ሆኖ የተመዘገበላት ሳኡዲ አረቢያ የዛሬው ድሏ የአለም ዋንጫ ጉዞዋ ዘለግ ያለ እንዲሆንም መነቃቃት እንደሚፈጥር ይጠበቃል።
አርጀንቲና በአለም ዋንጫው 18 ጊዜ ተሳትፋ የ1978ቱን እና የ1986ቱን ዋንጫ ወስዳለች።
ሳኡዲ አረቢያ በበኩሏ የስድስት ጊዜ ተሳትፎ ነው ያላት። ሳኡዲ ድሉን ተከትሎ ምድብ ሶስትን በአንደኝነት እየመራች ነው።
ከምድቡ ሜክሲኮ ከፓላንድ የሚያደርጉት ጨዋታ ምሽት 1 ስአት ይደረጋል።