ሜሲከ36 ዓመት በኋላ ሀገሩን ወደ ዋንጫ እንዲመልስ ... እድል ወይስ ብቃት?
ሁለት የአለም ዋንጫዎችን ያነሳችው የሊዮኔል ሚሲ ሀገር አርጀንቲና ብሄረዊ ቡድን ዝግጅት ምን ይመስላል
የነማራዶና ሀገር እንደ ሜሲ ያሉ ተተኪዎችን ብታፈራም ወደ ቦነሰአይረስ ዋንጫውን የሚወስድላት እየናፈቀች ሶስት አስርት አልፈዋል
ሊጀመር አምስት ቀናት የቀሩት የኳታር አለም ዋንጫ ለፈጣኑ አርጀንቲናዊ አጥቂ ከባድ ጫና ይዞ መጥቷል።
የአለም ዋንጫውን ዶሃ ላይ መውሰድ አልያም የመጨረሻውን እድል ማባከን፤ የሃገሩን ስኬት አለመመለስም የሚያጎድልበት ብዙ ነውና ጫናው በዝቶበታል።
የነዲያጎ ማራዶና ሀገር አርጄንቲና አሁን ድል ይራቃት እንጂ ኡራጓይ ባዘጋጀችው የመጀመሪያ የአለም ዋንጫ ለፍፃሜ በመድረስ የኳስ አሽሞንሟኞች ሀገር መሆኗን ማሳየት ጀምራለች።
በአለም ዋንጫ ተሳትፎም የሚቀድሟት ብራዚል፣ ጀርመንና ጣሊያን ናቸው፤ በአለም ዋንጫ ያልተሳተፉት አራት ጊዜ ብቻ ነው።
አርጀንቲና በአለም ዋንጫው አምስት ጊዜ ለፍፃሜ ደርሳ ሁለት ጊዜ ድል ተቀዳጅታለች፤ በፈንጆቹ በ1978 እና በ1986 ነበር።
ውሃ ሰማያዊና ነጭ ለባሾቹ ሜክሲኮ ያዘጋጀችውን የ1986 የአለም ዋንጫ እንዲያነሱ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና የአምበሳውን ድርሻ ወስዷል።
ከአራት አመት በኋላ ግን በሜክሲኮ ሽንፈትን ያስተናገደችው ምዕራብ ጀርመን የማራዶናን ሀገር አሸንፋ ዋንጫ አነሳች።
በ2014ቱ የማራካኛ ስታዲየም ፍልሚያ የግምብ አጥሯን አፍርሳ የተዋሃደችው ጀርመን አርጀንቲናን አሸንፋ ዋንጫ ስታነሳ ውሃ ሰማያዊዬቹ በሀገር ቤትም በውጭም ጥያቄ ይነሳባቸው ጀመር።
ከብራዚሉ 5ኛ የፍፃሜ ጨዋታ በፊትም ሆነ በኋላ ብሄራዊ ቡድኑ በአውሮፓ ኮከቦች የተገነባ ቢሆንም አሳማኝ የዋንጫ ቡድን ሆኖ መቅረብ ተስኖታል የሚሉ ቅሬታዎች ይነሱበታል።
ብሄራዊ ቡድኑ በ81 የአለም ዋንጫ ጨዋታዎች 47 ድሎች ቢያስመዘግብም እንደ ማራዶና አይነት ለድል ታግሎ ዋንጫን ወደ ቦነሳይረስ የሚወስድ ተጫዋችን በመናፈቅ አመታት ተቆጥረዋል።
የአለም የእግር ኳስ ምትሃተኛው ሊዮኔል ሜሲም እድል ፊቷን አዙራበትም ይሁን በሌላ ምክንያት የማራዶናን ሌጋሲ ማስቀጠል አልቻለም።
የሰባት ባሎንዶር አሸናፊው ሜሲ ለአምስተኛ ጊዜ የሚያደርገው የአለም ዋንጫ ሀገሩን ከ36 አመታት የድል ጥማት በኋላ ወደ ድል እንዲመልስ ይጠበቃል።
የ35 አመቱ ሜሲ በ2014 የሚችለው ጥረት አድርጎ ለዋንጫ ቢያደርስም አልተሳካለትም።
በ2016ቱ የኮፓ አሜሪካ ፍፃሜ በቺሊ ከተሸነፉ በኋላ ለብሄራዊ ቡድን ጨዋታ አልተፈጠርኩም፤ በቃኝ እስከማለት ደርሶ እንደነበር የሚታወስ ነው።
በዚህ ወሳኝ ጨዋታ የመጀመሪያውን መለያ ምት መሳቱም ዳግም ወደ ቡድኑ የመመለስ ስነልቦናውን ይጎዱታል ቢባልም በሩስያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የአለም ዋንጫ ተሳትፏል።
የመጨረሻው ይሆናል በተባለው የኳታሩ የአለም ዋንጫም ቡድኑን እየመራ ለተናፋቂው ድል ይፋለማል።
ሜሲ በእግር ኳስ ህይወቱ ካስቆጠራቸው 784 ጎሎች ውስጥ በአለም ዋንጫ ጨዋታዎች ያስቆጠራቸው ስድስት ጎሎችን ብቻ ነው።
የአለም ዋንጫው የታላቅነት መጨረሻ መለኪያ ሚዛን ሆኖ የሜሲን የአመታት የስኬት ታሪክ የሚያጠፋ አይደለም፤ ዋንጫውን ማንሳት ያለው ክብር ታላቅነቱ ሳይዘነጋ።
ማራዶና ራሱ በ2010 ቡድኑን በአሰልጣኝነት ይዞ ዋንጫውን አላነሳም የሚሉ የሜሲ አድናቂዎች ግን ከእድል ማጣት ጋር በማያያዝ ዘብ ይቆሙለታል።
አርጀንቲና ቀናት በቀሩት የኳታር የአለም ዋንጫ ከሳኡዲ አረቢያ፣ ሜክሲኮ እና ፖላንድ ጋር በምድብ ሶስት ተደልድላለች።
ከምድቡ በቀላሉ እንደሚያልፉ ግምት የተሰጣቸው ውሃ ሰማያዊ ለባሾቹ አሰልጣኝ ሊዮኔል ስካሎኒ በከዋከብት የተሞላ ቡድን ይዘው ወደ ኳታር ያቀናሉ።
የጁቬንቱሱ ኤንጅል ዲማሪያ እና የሮማው ፓውሎ ዲባላ የፊት መስመሩን ከሜሲ ጋር ይመራሉ። አምስት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾችም በስካሎኒ ስብስብ ተካተዋል።
አርጀንቲና ዘንድሮ ለ22ኛ ጊዜ በሚካሄደው የአለም ዋንጫ ምን ውጤት ታስመዘግባለች ብለው ይገምታሉ?