ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለሳዑዲው አል ናስር በተከታታይ 4 ጨዋታዎች ጎል ማስቆጠር ችሏል
ፖርቹጋላዎው ኮከብ ክርስቲያ ሮናልዶ የሳዑዲ አረቢያን እግር ኳስ በማነቃቃት ውስጥ ፈር ቀዳጅ በመሆኑ ኩራት እንደሚሰማው አስታወቀ።
የ38 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ የእግር ኳስ ኮከብ በሁለት ዓመት ከግማሽ ስምምነት የሳዑዲውን አል ናስር መቀላቀሉን ተከትሎ ታላላቅ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንዲጓዙ በር ከፍቷል።
በራዚላዊው ኮከብ ኔይማር ጁኒየር፣ የ2022 የባላድኦር አሸናፊው ፈረሳያዊው ኮከብ ካሪም ቤንዜማ፣ የአፍሪካ የዓመቱ ኮከብ እግር ኳስ ተጫዋች ሳዲዮ ማኔ፣ የቀድሞ ሊቨርፑል አምበል ጆርዳን ሄንደርሰን፣ የቀድሞ የቼልሲ ተጫዋች ኒጎሎ ካንቴ የሳዑዲ አረቢያ ክለቦችን ከተቀላቀሉ ተጫዋቾች ውስጥ ተጠቃሾቹ ናቸው።
ሮናልዶ ባሳለፍነው ሳምንት በሰጠው መግለጫ፤ “ከ6 ወር በፊት ወደ ሳዑዲ የመሄድ ውሳኔዬ እንደ እብደት ይታይ ነበር አሁን ግን የተለመደ ነገር ሆኗል” ብሏል።
“አሁን ላይ በሳዑዲ ሊግ ውስጥ መጫወት የተለመደ እና መደበኛ እየሆነ መጥቷል፤ ይህ እንደሚሆን አስቀድሜ አውቅ ነበር፣ እንደ አል ናሰር ተጫወችነቴ ለ8 ወራት ተጫውቻለሁ፣ መሻሻሎችንም እያስተዋልኩ ነው” ብሏል።
ፖርቹጋላዊው ኮከብ ሮናልዶ ባለፉት ተከታታይ አራት ጨዋታዎች ላይ አራት ጎሎችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን፤ ሮናልዶ የሊጎን ከፍተኛ ግብ አግቢነትም እየመራ ይገኛል።
“ሰዎች ስለ ሳዑዲ አረቢያ እና ስለ ሀገሪቱ ባህል ያላቸው አመለካከት እየተወለጠ መምጣቱን በማየቴ ኩራት ይሰማኛል” ያለው ሮናልዶ፣ ከዚህ በተጨማሪም “አሁን ላይ የሳዑዲ የእግር ኳስ ደረጃ ከፍተኛ ሆኗል፤ ይህ ደስተኛ ያደርገኛል” ብሏል።
“የሳዑዲ አረቢያ እግር ኳስን በማነቃቃት ፈር ቀዳጅ ነበርኩ እናም በዚህ ኩራት ይሰማኛል፤ የሳውዲ ሊግ በሚቀጥሉት አመታት እድገቱ እንዲቀጥል እና አስደናቂ ከፍተኛ ሊግ እንዲሆን እፈልጋለሁ” ሲልም ተናግሯል።
ስል ረጅም ጊዜ ተቀናቃኙ ሊዮኔል ሜሲ የተጠየቀው ሮናልዶ፤ “ነገሮችን እንደዛ አላያቸውም፣ መድረኩን ለ15 ዓመታት ተጋርተናል፤ ጓደኛሞች ነን አልልም ግን እርስ በርሳችን እንከባበራለን” ብሏል።
“ከሜሲ ጋር የነበረው ፉክክር በጣም ጥሩ ነበር፣ ደጋፊዎቹም ይወዱታል” ያለ ሲሆን፤ “ክርስቲያኖን ከወደዳችሁ ሜሲን የምትጠሉበት ምንም ምክንያት የለም” ሲልም ተናግሯል።
ሁለቱም ተጫዋቾች የእግር ኳስን ታሪክ ቀይረዋል እና ክብር ይገባቸዋል ሲል የገለጸው ሮናልዶ፤ አሁን ላይ በክርሲያኖ ሮናልዶ እና በሜሲ መካከል ያለው የፉክክር ዘመን አብቅቷል ሲልም አስታውቋል።