አርጀንቲና በመለያ ምት 4 ለ 2 ፈረንሳይን አሸንፋለች
በሉሳይል ስታዲየም የተደረገው ልብ አንጠልጣይ ፍልሚያ በአርጀንቲና አሸናፊነት ተደምድሟል።
አርጀንቲና ሶስት ጊዜ መርታ አቻ በሆነችበት ምሽት ሌዮኔል ሜሲ ሁለት ጎሎችን አስቆጥሯል።
ውሃ ሰማያዊ እና ነጭ ለባሾቹ በመጀመሪያው አጋማሽ 2 ለ 0 እየመሩ ቢወጡም ፈረንሳይ በኪሊያን ምባፔ የ80 እና 81ኛ ደቂቃ ሁለት ጎሎች አቻ ሆናለች።
በተጨማሪ 30 ደቂቃውም ሜሲ ሶስተኛውን ጎል ለሀገሩ ቢያስቆጥርም የፈረንሳዩ የ23 አመት ኮከብ ኪሊያን ምባፔ ባስቆጠራት ሶስተኛ ጎል ጨዋታው በመለያ ምት ተጠናቋል። በዚህም አርጀንቲና 4 ለ 2 በሆነ የፍጹም ቅጣት ምት ጎል አሸናፊ ሆናለች።
ሊዮኔል ሜሲ ከ36 አመት በፊት ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ያሳካውን ክብር በደገመበት ምሽት የብራዚላዊውን ፔሌ የጎል አስቆጣሪነት ክብር ማሻሻል ችሏል።
የ35 አመቱ ሜሲ በ26 የአለም ዋንጫ ጨዋታዎች ተሰልፎ 13 ጎሎችን በማስቆጠሩም በብራዚላዊው ፔሌ ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን ማሻሻል ችሏል።
አርጀንቲና በዛሬው የሉሳይል ስታዲየም ፍልሚያ ድል ማድረጓን ተከትሎ በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታ ተሸንፋ (በሳኡዲ አረቢያ) ዋንጫውን በመውሰድ ስፔን በ2010 የያዘችውን ሪከርድ ተጋርታለች።
የላቲን አሜሪካዋ ሀገር ፈረንሳይን በመርታት ሶስተኛ ዋንጫዋን አንስታለች።
አርጀንቲና በ1978 ፣ 1986 እና በኳታር የዓለም ዋንጫን ወስዳለች።