በ11 የአለም ዋንጫዎች ላይ የታደሙት ብራዚላዊ
የመጀመሪያ የአለም ዋንጫ ጨዋታን በአርጀንቲና በ1978 የተመለከቱት ዳኔል ስብሩዚ በኳታርም የአለም ዋንጫ ጨዋታዎችን ተከታትለዋል
“የአለም ዋንጫን መመልከት ከአዳዲስ ባህልና ልምድ ጋር መተዋውቅ ነው ፤ በ2026ቱ የአለም ዋንጫ ለመታደምም ዝግጁ ነኝ” ብለዋል
11 የአለም ዋንጫዎችን የተመለከቱት ብራዚላዊ በድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ስማቸውን ማስፈር ችለዋል።
ዳኔል ስብሩዚ የተባሉት የ76 አመት አዛውንት የሳኦሎ ከተማ ነዋሪ ናቸው።
ስብሩዚ በ1978 ወደ አርጀንቲና በማቅናት የመጀመሪያ የአለም ዋንጫ ጨዋታን ከተመለከቱ ወዲህ አለምን በኳስ ምክንያት ዞረዋል።
የዘንድሮውን የኳታር የአለም ዋንጫ ለመታደምም ዶሃ ገብተው ሰንብተዋል።
የ76 አመቱ አዛውንት በዶሃ 11ኛ የአለም ዋንጫ ጨዋታን ሲመለከቱም የአለም የድንቃድንቅ መዝገብ ክብረወሰን ይዘዋል በሚል የምስክር ወረቀት ሰጥቷቸዋል።
የአለም ዋንጫን መመልከት ከአዳዲስ ባህልና ልምድ ጋር መተዋውቅ ነው የሚሉት ስብሩዚ ፤ የአለም ዋንጫ ከመልከ ብዙ ተሰጥኦ ባለቤቶች ጋር የሚያገናኝ መድረክ መሆኑን አንስተዋል።
ከአርጀንቲና እስከ ኳታር አለም ዋንጫን ለመመልከት ሲጓዙም የብራዚልን ባህልና ወግ ሲያስተዋውቁ እንደነበር ተናግረዋል።
ባለፉት 44 አመታት በተለያዩ አልባሳት አጊጠው ብራዚልን እየደገፉ የሳኦ ፖሎን ባህል በስፋት ያስተዋወቁት ስፖርት አፍቃሪ፥ የአለም ዋንጫን በስታዲየም ከመመልከት የሚያስቆመኝ ሞት ብቻ ነው እያሉ ነው።
አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጋራ በሚያዘጋጁት የ2026 የአለም ዋንጫ ለምታደምም ፍላጎታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በራሳቸው የተያዘውን ክብረወሰን ለማሻሻል ተስፋ አድርገዋል።