ፈረንሳይ የዓለም ዋንጫ ግርግርን በመፍራት 14 ሽህ ወታደሮችን አሰማራች
የጸጥታ ኃይሎች እሁድ ምሽት ለሚደረገው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ግጥሚያ ደህንነትን ለመጠበቅ ይሰማራሉ ተብሏል ፈረንሳይ በሞሮኮ እና በክሮሺያ መካከል የዓለም ዋንጫ ሦስተኛ ደረጃን ለመያዝ ለሚደረገው ጨዋታም 12 ሽህ 800 የፖሊስ መኮንኖች መድባለች
የጸጥታ ኃይሎች እሁድ ምሽት ለሚደረገው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ግጥሚያ ደህንነትን ለመጠበቅ ይሰማራሉ ተብሏል
የዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ጨዋታ በፈረንሳይ እና አርጀንቲና መካከል በኳታር የሚካሄድ ቢሆንም ፓሪስ ከፍተኛ የፖሊስ ኃይል በግዛቷ ለማሰማራት በዝግጅት ላይ ናት ተብሏል።
የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር ጄራልድ ዳርማኒን እንዳስታወቁት 14 ሽህ የሚጠጉ የፖሊስ ኃይሎች በመላ ሀገሪቱ ይሰማራሉ። ፖሊሶቹ እሁድ ምሽት ለሚደረገው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ግጥሚያ ደህንነትን ለመጠበቅ ይሰማራሉ ብለዋል።
ሚንስትሩ ከነገ በስቲያ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች ወደ ጎዳናዎች ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል። የፈረንሳይ የዜና እንደዘገቡት በፓሪስ እምብርት የሚገኘውና የንግድ ማዕከሉ ታዋቂው ሻምፕ-ኤሊሴስ ለትራፊክ ዝግ ይሆናል።
ፈረንሳይ በዚህም ሳታበቃ ቅዳሜ በሞሮኮ እና በክሮሺያ መካከል የዓለም ዋንጫ ሦስተኛ ደረጃን ለመያዝ ለሚደረገው ጨዋታም 12 ሽህ 800 የፖሊስ መኮንኖች መድባለች። ሀገሪቱ ጥቃት እንዳይደርስ ከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ ለማድረግ ማቀዷ ተነግሯል።
ለዚህም ምክንያቱ በፈረንሳይ ተሸንፋ ከዋንጫው የተገለለችው ሞሮኮ ብዙ ቁጥር ያላቸው የሞሮኮ ተወላጆች በፈረንሳይ በመኖራቸው ነው ተብሏል።
ፈረንሳይ ከትናንት በስቲያ ረቡዕ በተካሄደው የዓለም ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ውድድር ሞሮኮን ካሸነፈች በኋላ በመላ ሀገሪቱ ረብሻ ታይቷል የተባለ ሲሆን፤ የፈረንሳይ ፖሊስ በዋና ከተማዋ ፓሪስ 167 ሰዎችን ጨምሮ ከ260 በላይ ሰዎችን ማሰሩ ተነግሯል።
የፊታችን እሁድ የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ከአርጀንቲና ጋር የዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ጨዋታ ያደርጋል። ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ ለዋንጫ የደረሱት ዶሮዎቹ በታሪካቸው ሦስተኛውን የዓለም ዋንጫ ለማንሳት ይፋለማሉ።