የመጀመሪያ የፍቅር ቀጠሮ ዕለት መክፈል ያለበት ማን ነው?
በጋራ ለተዝናናንበት ወጪ ብቻዬን መክፈል የለብኝም ያለው ግለሰብ ክስ መስርቷል
ወጪ አልጋራም ያለችው እንስትም ወንዱን በመዝናኛው ስፍራ ጥላ ሄዳለች ተብሏል
የመጀመሪያ የፍቅር ቀጠሮ ዕለት መክፈል ያለበት ማን ነው?
የሰው ልጆች አኗኗር በየጊዜው እንደ ወቅቱ ይቀያየራል። ቴክኖሎጂ ደግሞ ህይወትን ቀለል ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል አንዱ ነው።
በዚህም መሰረት ሩጫ ለበዛበት ዓለም ሰዎች ስራዎቻቸውን፣ ማህበራዊ መስተጋብራቸውን ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው ያሰናስላሉ።
ብዙዎች በይነ መረብን ተጠቅመው ወደ ፍቅር ከመግባት ጀምሮ ቤተሰብ እስከመመስረት እና ለዓመታት የዘለቁ ወዳጅነትን ያፈራሉ።
በሀገረ ሩሲያም በይነ ሙረብን ተጠቅመው በማህበራዊ ትስስር ገጾች ትውውቅን ፈጥረው ግንኑነታቸው ወደ ፍቅር ለማሳደግ ይስማማሉ።
እነዚህ ሰዎችም በሞስኮ ባለ አንድ መዝናኛ ስፍራ በአካል ለመገናኘት ቀነ ቀጠሮ ይይዛሉ።
በቀጠሯቸው መሰረት የተገናኙት እነዚህ የወደፊት ተስፈኞች ሲያወሩ፣ ሲተዋወቁ እና ሲዝናኑ ቆይተው የተዝናኑበት ሂሳብ ሲመጣ ግን ግጭት ውስጥ ይገባሉ።
ወንዱ በጋራ የተዝናኑበትን ሂሳብ ወጪ በጋራ እንዲከፍሉ ሀሳብ ቢያቀርብም እንስቷ ግን ወጪውን የመጋራት ፍላጎት እንደሌላት እና መክፈል ያለብህ አንተ ነህ በሚል ሀሳቧ ትጸናለሽ።
በመጨረሻም እንስቷ የመዝናኛ ስፍራውን ለቃ መሄዷን ተከትሎ ወንዱ 16 ሺህ የሩሲያ ሩብል ወይም 165 ዶላሩን ይከፍላል።
ወጪው በዝቶብኛል ግማሹን ክፍያ እሷ መክፈል ነበረባት ያለው ይህ ሰውም ጉዳዩን ይዞ ወደ ፖሊስ ጣቢያ አምርቷል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል።
ክስ የቀረበለት የሞስኮ ፖሊስ ጣቢያም በምን መልኩ ለአመልካች ምላሽ እንደሚሰጥ እያሰበበት መሆኑን አስታውቋል ተብሏል።