የፍቅረኞችን ታማኝነት የሚፈትነው መተግበሪያ
መተግበሪያው በእስያ በርካታ ደንበኞችን ያፈራ ሲሆን በክፍያ እና በነጻ አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል
የፍቅረኛቸው ታማኝነት እንዲረጋገጥላቸው የሚፈልጉ ደንበኞች እስከ ስምንት ዶላር ይከፍላሉ
የፍቅረኛን ታማኝነት የሚፈትነው መተግበሪያ
ማህበራዊ የትስስር ገጾች ከሚሰጧቸው መልካም አገልግሎቶች መካከል መረጃን መለዋወጥ፣ ከተጠፋፉ ሰዎች ጋር መገናኘት፣ አዳዲስ ሰዎችን መተዋወቅ እና ሌሎችም ዋነኞቹ ናቸው።
በርካቶችም ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው የህይወት ዘመን ወዳጅ እና ቤተሰብ አፍርተውበታል።
ይህ በዚህ እንዳለም ማህበራዊ ትስስር ገጾች የብዙዎችን ቤተሰብ እንዲበተን ምክንያት የሚሆኑበት አጋጠሚም ይፈጠራል።
በእስያዊቷ ቬትናም ፌስቡክን በመጠቀም የፍቅረኛቸውን ታማኝነት የሚፈትን አሰራር መዘርጋቱን ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ ሰዎች ፍቅረኛቸውን ለመፈተን ሲሉ በክፍያ ለዚህ ስራ በሚል ከተቋቋሙ ድርጅቶች ጋር እየሰሩ ነው።
እነዚህ ድርጅቶችም እንዲፈትኑ የተነገራቸውን ሰው ታማኝነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ስልቶችን እንደሚጠቀሙ ተገልጿል።
ድርጅቶቹ ከሚጠቀሟቸው ስልቶች መካከልም አማላይ ፎቶዎችን መላክ፣ የጽሁፍ እና ሌሎች መልዕክቶችን መላክ ዋነኞቹ ናቸው።
በዚህ ስራ ከተሰማሩ ግለሰቦች መካከል የ27 ዓመቱ ማንህ ሁንግ አንዱ ሲሆን በቅርቡ 30 ደንበኞቹ ፍቅረኞቻቸውን እንዲፈትንላቸው አመልክተው 26 ፍቅረኞች ታማኝ አለመሆናቸውን ለደንበኞቼ አረጋግጫለሁ ብሏል።
የተለያዩ ቋንቋዎችን፣ ቦታዎችን እና ምስሎችን በመጠቀም የደንበኞችን ጥያቄ የሚመልሰው ይህ ግለሰብ ብዙዎቹ በወጥመዱ እንደሚወድቁም ተናግረዋል።
ለዚህ አገልግሎቱም በአንድ ሰው ስምንት ዶላር በመቀበል አገልግሎቱን እየሰጠ መሆኑንም አስታውቋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከቬትናም ውጪ ያሉ ደንበኞችን እያፈራ መሆኑን የሚናገረው ይህ ግለሰብ ፍቅረኛሞች፣ ባልና ሚስቶች ዋነኛ ደንደኞቹ መሆናቸውንም አክሏል።
የስነ ልቦና ባለሙያዎች ግን እንዲህ አይነቱን የታማኝነት ፈተናን የነቀፉ ሲሆን አለመተማመን ለፍቅር እና ቤተሰብ መጎዳት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።