ሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸውን ለድርድር እንደሚልኩ አረጋግጠዋል
አርሜኒያ እና አዘርባጃን በሩሲያ ሊደራደሩ ነው
አርሜኒያ እና አዘርባጃን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸውን ለድርድር ሞስኮ እንደሚልኩ ማረጋገጣቸውን አርአይኤ የዜና ወኪል የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ጠቅሶ ዘግቧል ፡፡
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በናጎርኖ-ካራባክ ግጭት ወታደራዊ እርምጃዎች እንዲቆሙ ጥሪ ባቀረቡበት ወቅት ፣ የክሬምሊን ጥሪ ለአርበጃጃን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀይሁን ባይራሞቭ እና ለአርሜንያው አቻቸው ለዞህራብ ምናትሳካንያን ደርሷል፡፡
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ እንዳሉት ሁለቱም ሀገራት ጥሪውን ተቀብለዋል፡፡ ድርድሩ መች እንደሚካሔድ ባይገለጽም ለድርድሩ ዝግጅቶች እየተደረጉ እንደሆነ ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
ክሬምሊን ሐሙስ ዕለት ባወጣው መግለጫ ፣ ከአዘርባጃን ፕሬዝዳንት ኢልሀም አሊዬቭ እና ከአርሜኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኒኮል ፓሺንያን ጋር የሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን ተከታታይ የስልክ ውይይቶችን ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው የናጎርኖ-ካራባክ ግጭት እንዲቆሙ ጥሪ የቀረበው፡፡
ባለፉት 12 ቀናት ውስጥ ከ400 በላይ ሰዎችን የቀጠፈው የናጎርኖ-ካራባክ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት በሚደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት የአሁኑ የመጀመሪያው የስኬት ጭላንጭል የታየበት ነው፡፡
በጦርነቱ ቀጣይነት እና በአካባቢው በነገሰው ከፍተኛ ውጥረት የተነሳ በተለይ ሩሲያ ፣ አሜሪካ እና ፈረንሳይ ተዋጊዎቹን ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለማምጣት ተደጋጋሚ ጥረቶችን አድርገዋል፡፡