የአዘርባጃን እና የናጎርኖ-ካራባክ ትልልቅ ከተሞች በከባድ መሳሪያዎች ተደብድበዋል
የናጎርኖ-ካራባክ ጦርነት ተባብሶ ቀጥሏል
በአወዛጋቢው የናጎርኖ-ካራባክ ግዛት ጉዳይ በአርሜኒያ እና አዘርባጃን መካከል የተጀመረው ከባድ ጦርነት የቀጠለ ሲሆን የአዛርባጃን ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ጋንጃ በአርሜንያ ጦር ተደብድባለች፡፡
የጸቡ መንስኤ የሆነው አከባቢ በይፋ የአዘርባጃን አካል ቢሆንም ነገር ግን በአርመናውያን ጎሳ የሚተዳደር ነው፡፡
እራሳቸውን የሾሙት የናጎርኖ-ካራባክ ባለሥልጣናት የአዘርባጃን ኃይሎች የግዛቲቱን ዋና ከተማ ስቴፓናከርትን ከደበደቡ በኋላ የጋንጃን ወታደራዊ አውሮፕላን ማረፊያ መምታታቸውን ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ አዘርባጃን ምንም የጋንጃ ወታደራዊ ጣቢያዎች አልተመቱብኝም ስትል አስተባብላለች፡፡
በአዘርባጃን ተርተር ከተማ ጥቃት የደረሰበት ቤት
ከሳምንት በፊት የሁለቱ አካላት ግጭት ከተጀመሩ ወዲህ ከ 230 ሰዎች በላይ ስለመሞታቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከሁለቱም ወገኖች የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ በገለልተኛ ወገን ማጣራት ቢካሔድ ህይወታቸውን ያጡ ወታደሮች እና ሲቪሎች ቁጥር ከሚገመተው በላይ ሊሆን እንደሚችል ዘገባዎች እየጠቆሙ ነው፡፡
አርሜኒያ እና አዘርባጃን እ.ኤ.አ. ከ 2016 ወዲህ በመካከላቸው ለተከሰተው ከባድ ግጭት እርስ በርሳቸው እየተወነጃጀሉ ነው፡፡
የአዘርባጃን ጦር ውጊያው ከተጀመረበት ካለፈው እሁድ እለት ጀምሮ ሰባት መንደሮች መልሶ መቆጣጠሩን የገለጸ ሲሆን ናጎርኖ-ካራባክ ደግሞ ወታደሮቹ የግምባር ላይ አቅማቸውን “አሻሽለዋል” ብሏል፡፡
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አርሜኒያ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ከፈረንሣይ ፣ ከሩሲያ እና ከአሜሪካ አስታራቂዎች ጋር “ለመሳተፍ ዝግጁ” መሆኗን ገልፃለች፡፡
በግልፅ በቱርክ የምትደገፈው አዘርባጃን በበኩሏ የአርሜኒያ ወታደሮች ከናጎርኖ-ካራባክ እና ከተቆጣጠሯቸው ሌሎች አጎራባች አካባቢዎች ለቀው ካልወጡ በስተቀር ስምምነት እንደማይታሰብ አስታውቃለች
ሁለቱ የቀድሞ የሶቪዬት ሪፐብሊኮች እ.ኤ.አ. ከ1989 - 1994 በግዛቲቱ ጉዳይ ተዋግተው በመጨረሻም የተኩስ አቁም አወጁ፡፡ ሆኖም በግጭቱ ዙሪያ እልባት አግኝተው አያውቁም፡፡
አሁንም መስማማት ተስኗቸው የቀጠሉት ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ የሚገኝ ሲሆን የአዘርባጃን መከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ እሁድ መስከረም 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው አጭር መግለጫ እንዳመለከተው የአርሜኒያ ጦር ከናጎርኖ-ካራባክ በስተ ሰሜን በሚገኘው የምዕራብ አዘርባጃን ከተማ ጋንጃ ላይ በጥይት ድብደባ ፈጽሟል፡፡ “ይህ ግጭቱ እንዲቀጥል የተፈጸመ ጸብ አጫሪ ድርጊት ነው” ያሉት ሚኒስትሩ ዛካሪ ሃሳኖቭ በዚህም የንጹሀን ህይወት ሲያልፍ ንብረታቸው እና ታሪካዊ ስፍራዎች ስለመውደማቸው ይፋ አድርገዋል፡፡
ፖለቲካ በአዘርባጃን ጋንጃ ከተማ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ህንጻዎች መውደማቸው ተገልጿል
አርሜኒያ ድርጊቱን አልፈጸምኩም ያለች ሲሆን የናጎርኖ-ካራባክ አመራሮች በዋና ከተማቸው ስቴፓናከርት ላይ ለተፈጸመው ጥቃት በቀል የፈጸሙት ድብደባ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን የደበደቡት ግን የአዘርባጃንን የጦር አውሮፕላን ማረፊያ እንደሆነ ነው ያሳወቁት፡፡
በናጎርኖ-ካራባክ ከተማ-ስቴፓናከርት ጉዳት የደረሰበት አፓርታማ
የተለያዩ ሀገራት ሁለቱን ወገኖች ለማሸናገል የሚያደርጉት ሙከራ እስካሁን ዉጤት ማምጣት አልቻለም፡፡ ይሁንና የሁለቱም ሀገራት ዜጎች ጦርነቱ እንዲቆም በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
ናጎርኖ-ካራባክ - ቁልፍ እውነታዎች-ከቢቢሲ
• 4,400 ስ. ኪ.ሜ. (1,700 ስ.ማይል) ያህል ተራራማ አካባቢ ነች
• በተለምዶ ክርስቲያን አርመናውያን እና ሙስሊም ቱርኮች ይኖሩባታል
• በሶቪየት ዘመን በአዘርባጃን ሪፐብሊክ ውስጥ ራሱን የቻለ ግዛት ሆነች
• በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአዘርባጃን አካል ሆኖ እውቅና የተሰጠው ቢሆንም አብዛኛው ህዝቧ የአርሜኒያ ብሄረሰብ ነው
• የግዛቲቱ የራስ-አስተዳደር ባለሥልጣናት አርሜንያን ጨምሮ በማንኛውም የተባበሩት መንግስታት አባላት ዕውቅና አልተሰጣቸውም
• እ.ኤ.አ. ከ1988 - 1994 በቆየው ጦርነት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች ሲፈናቀሉ ወደ 30,000 ያህሉ ተገድለዋል
• የተገንጣይ ኃይሎች አዘርባጃን ውስጥ በተከበበው አካባቢ አንዳንድ ተጨማሪ ግዛቶችን ተቆጣጠሩ
• ከ 1994 የተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ ውዝግብ ተባብሶ ቀጥሎባታል
• ቱርክ አዘርባጃንን በግልጽ ትደግፋለች
• ሩሲያ በአርሜኒያ የጦር ሰፈር አላት