ዛሬ በተከሰተው ግጭት ከሁለቱም ወገን የሰዎች ህይወት ማለፉ ተገልጿል
በአርሜኒያ እና በአዘርባጃን መካከል ግጭት መቀስቀሱ ተዘገበ
ዛሬ እሁድ መስከረም 17 ቀን 2013 ዓ.ም በአርሜኒያ እና በአዘርባጃን መካከል በናጎርኖ-ካራባክ አወዛጋቢ ስፍራ ግጭት የተቀሰቀሰ ሲሆን ይህም በደቡብ ካውካሰስ መረጋጋት ላይ ስጋት ፈጥራል፡፡
አካባቢው ነዳጅ እና ጋዝን ወደ ዓለም ገበያዎች የሚያጓጉዙ መተላለፊያ የቧንቧ መስመሮች የሚገኙበት መሆኑ ደግሞ ስጋቱን ያባብሰዋል፡፡
ከዚህ ቀደም እ.ኤ.አ. በ 1990 ዎቹ ጦርነት ያካሄዱት ሁለቱም ወገኖች በተፈጠረው ውጊያ የሰዎች ህይወት ማለፉን አስታውቀዋል፡፡ በአዘርባጃን ውስጥ የሚገኝ እና በአርመኖች ብሄረሰብ የሚተዳደረው ናጎርኖ-ካራባክ የተሰኘ ተገንጣይ ክልል አመራሮች ወታደራዊ አዋጅ በማወጅ ወንዶቻቸውን ለውጊያ ማዘጋጀታቸውን አዘርባጃን ስለመግለጿ የሮይተርስ ዘገባ ያሳያል፡፡
ይህን ተከትሎ አዘርባጃን በናጎርኖ-ካራባክ ላይ የአየር እና የመድፍ ጥቃት አድርሳለች ስትል አርሜኒያ ትከሳለች፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ዉጊያ አዘርባጃን ለአርሜኒያ ጥይት ምላሽ እንደ ሰጠች እና እስከ ሰባት መንደሮችን እንደተቆጣጠረች ብትገልጽም የግጭቱ መንስኤ ናጎርኖ-ካራባህ ይህንን አስተባብሏል፡፡
በአብዛኛው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሚገኙባት አርሜኒያ እና በዋነኝነት የእስልምና እምነት ተከታዮች ሀገር በሆነችው አዘርባጃን መካከል የተፈጠረው ግጭት እንዲረግብ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጀምረዋል፡፡ ሩሲያ አፋጣኝ የተኩስ አቁም ጥሪ ያቀረበች ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ደግሞ ሁለቱ ሀገራት ለድርድር እንዲቀመጡ ጠይቀዋል፡፡ ፈረንሳይ ፣ ጀርመን እና የአውሮፓ ህብረት ሀገራትም ሁለቱ ሀገራት ችግራቸውን በድርግር እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሁለቱም ሀገራት እ.ኤ.አ. በ1991 ከመፍረሷ በፊት የሶቪየት ህብረት አካል ነበሩ፡፡
ናጎርኖ-ካራባህ የሶቪየት ህብረት በ 1991 ስትፈርስ በተቀሰቀሰ ግጭት ከአዛርባጃን የተገነጠለ ግዛት ነው፡፡
እ.ኤ.አ. በ 1994 የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረግም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከተገደሉ እና ብዙ ሰዎች ከተፈናቀሉ በኋላ አዘርባጃን እና አርሜኒያ በተደጋጋሚ በናጎርኖ-ካራባክ እና በድንበሮቻቸው ጥቃት ተፈጽሞብኛል በሚል እስከ አሁንም እርስ በርሳቸው ይካሰሳሉ፡፡
በዛሬው ግጭት ከሁለቱም ወገን ንፁኃንን ጨምሮ የሰዎች ህይወት ማለፉ ቢገለጽም ስለ ሞቱት ሰዎች ቁጥር እና ስለ ደረሰው አጠቃላይ ጉዳት ዝርዝር መረጃ አልወጣም፡፡