ስልኩን ለማውጣት ሲል 2 ሚሊየን ሊትር ውሃ ከግድብ ኢንዲፈስ ያደረገው ባለስልጣን እንዲታሰር ተወሰነ
ሕንዳዊው ባለስልጣን ራሱን በሰልፊ ፎቶ እያነሳ እያለ ነበር ከቀናት በፊት ስልኩ ወደ ግድቡ የገባበት
ይህ ባለስልጣን ስልኩን ለማውጣት ሲል የግድቡ ውሃ እንዲመጠጥ ማስደረጉን ተከትሎ መነጋገሪያ ሆኗል
በሕንድ የመስኖ ግድብ ዳርቻ ላይ በሞባይል ስልክ ራሱን በራሱ ፎቶ እያነሳ የነበረ አንድ ባለስልጣን ለስልኩ ሲል የግድቡን ዉሃ ማስመጠጡ ይታወሳል።
ይህ የምግብ ቁጥጥር ባለስልጣን 1 ሺህ 200 ዶላር ዋጋ ያለቀው ሳምሰንግ የእጅ ስልኩ ወደ ግድቡ ገብቶብኛል፣ ስልኩ በርካታ እጅግ አንገብጋቢ የመንግስት መረጃዎችን ይዟል በሚል ግድቡ እንዲመጠጥ አስደርጓል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ባለስልጣኑ መጀመሪያ ላይ ስልኩን ለማስወጣት በአካባቢው ያሉ ዋናተኞችን ቢያሰማራም አለመገኘቱን ተከትሎ በውሃ መሳቢያ ፓምፕ የግድቡ ውሃ እንዲመጠጥ አስደርጓል ተብሏል።
ራጂሽ ቪሽዋስ የተባለው ይህ ባለስልጣን ስልኩን ለማግኘት ሲባል 2 ሚሊየን ሊትር የግድቡን ውሃ ለማፍሰስ ሶስት ቀናት እንደፈጀባቸው ተገልጿል።
ይህን ተከትሎም የሐገሪቱ መንግስት ባለስልጣኑ በፈጸመው ድርጊት ስልጣኑን ያለ አግባበብ በመጠቀም ከስራ የታገደ ሲሆን ጉዳዩ አሁንም መነጋገሪያነቱን ቀጥሏል ተብሏል።
በዛሬው ዕለትም ይህ ለስልኩ ሲል አንድ ግድብ ውሃ ያስመጠጠው ባለስልጣን እንዲታሰር እና በህግ እንዲጠየቅ እንደተወሰነበት ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በመጨረሻም የባለስልጣኑ ስልክ ቢገኝም በውሃ ተሞልቶ የመስራቱ ነገር አጠራጣሪ ነው የተባለ ሲሆን ጉዳዩ በህንድ ዋነኛ መነጋገሪያ ሆኗል።
ለዚህ ባለስልጣን ሲባል እንዲመጠጥ እና እንዲባክን የተደረገው ውሃ ከስድስት ሺህ በላይ ሄክታር መሬት መስኖ የማልማት አቅም እንደነበረው ተገልጿል።