ሩሲያ በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት ምዕራባውያኑ በጣሉባት ማዕቀብ ምክንያት ለህንድ እና ቻይና ነዳጅ በቅናሽ እየሸጠች ነው
ህንድ ከሩሲያ የምታስገባው ድፍድፍ ነዳጅ በ10 እጥፍ መጨመሩ ተገልጿል።
የህንዱ ባሮዳ ባንክ ባወጣው ሪፖርት እንዳመላከተው፥ ኒውደልሂ በ2021ከውጭ ሀገራት ካስገባችው ነዳጅ የሩሲያ ድርሻ 2 በመቶ ብቻ ነበር።
በ2022 ግን በአስር እጥፍ አድጎ 20 በመቶውን ድርሻ ይዟል ነው ያለው ባንኩ።
ህንድ ባለፈው የፈረንጆቹ አመት ከሩሲያ ካስገባችው ነዳጅ ከእያንዳንዱ ቶን 89 የአሜሪካ ዶላር ቅናሽ ተደርጎላታል።
በዚህም የእስያ ሶስተኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤቷ ሀገር በ2022 5 ቢሊየን ዶላር ወጪ እንድታድን ማድረጉን ነው ባንኩ ያወጣው ሪፖርት ያሳየው።
ከዩክሬኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ ምዕራባውያን በሩሲያ የነዳጅ ንግድ ላይ ማዕቀብ መጣላቸው ይታወሳል።
ሞስኮ የተጣለባትን የነዳጅ ሽያጭ ማዕቀብ ለመቀልበስ እንደ ቻይና እና ህንድ ላሉ ሀገራት ነዳጅ በቅናሽ እየሸጠች መሆኑን የቢቢሲ ዘገባ ያሳያል።
ህንድ ከሞስኮ ነዳጅ እንዳታስገባ በአሜሪካ እና የአውሮፓ ሀገራት ጫና ቢደረግባትም በምዕራባውያኑ የተጣለውን የነዳጅ ማዕቀብ ወደጎን በማለት ከሩሲያ ጋር ወዳጅነቷን አጥብቃለች።
ኒውደልሂ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችውን ጦርነት በግልጽ አላወገዘችም የሚል ወቀሳም በተደጋጋሚ ይቀርብባታል።
የአለማችን ሶስተኛዋ ነዳጅ አስገቢ ሀገር ህንድ፥ የነዳጅ ፍላጎቷ ከፍተኛ መሆኑንና በድህነት ውስጥ የሚኖሩ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎቿን ፍላጎት ለማሟላት ከሌላ ሀገር በውድ የምገዛበት አቅም የለኝም ስትል ምዕራባውያኑን ትሞግታለች።
የዩክሬኑ ጦርነት እንደተጀመረ አውሮፓውያን ከሩሲያ የገዙት ነዳጅ ህንድ ካስገባችው በስድስት እጥፍ እንደሚበልጥ የህንድ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ሰበራሃይማንያም ጃይሻንካር ያወሳሉ።
“የመርህ ጉዳይ ከሆነ አውሮፓውያኑ ጦርነቱ እንደተጀመረ ወዲያውኑ ከሩሲያ ነዳጅ ማስገባታቸውን ለምን አላቆሙትም” ሲሉም ይጠይቃሉ።
15ኛ ወሩን የያዘው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት በአጭሩ የሚቋጭ አይመስልም የሚሉ ተንታኞች፥ ሩሲያም ማዕቀቦችን ለማለፍ ለእስያ አጋሮቿ ነዳጅ በቅናሽ ማቅረቧን እንደምትቀጥል እንደሚያምኑ ተናግረዋል።