በህንድ ድልድይ የሰረቁ ሌቦችን በፖሊስ እየተፈለጉ ነው ተባለ
ሌቦቹ ከባድ መሳሪያዎችን በመጠቀም በሁለት ቀናት ውስጥ ድለድዩን ቆራርጠው መውሰዳቸው ተነግሯል
ሌቦቹ ከ18 ሜትር በላይ ርዝመት ያለው የብረት ድልድይ ሰርቀዋል
የህንድ ፖሊስ የብረት ድልድይ የሰረቁ ሌቦችን እያፈላለገ መሆኑን በዛሬው እለት አስታውቋል።
ሌቦቹ ከ18 ሜትር በላይ ርዝመት ያለው የብረት ድልድይ መስረቃቸው የተነገረ ሲሆን፤ የሰረቁትን ድልድይ ብረት ቆራርጠው መሸጣቸው አልቀረም መባሉን ሮይተርስ ዘግቧል።
ድልድዩ የተሰረቀው ከፓንታ ግዛት ዋና ከተማ 150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አሚያዋር ገጠራማ መንደር መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል።
ዘራፊዎች ራቸውን በምስራቅ ቢሃር ግዛት ውስጥ ካለው የመስኖ ክፍል ጋር የተቆራኙ የመንግስት ባለስልጣናትን በመምሰል ጋዝ መቁረጫ እና ሌሎች ተንቀሳቃሽ ማሽነሪዎችን ተጠቅመው ድልድዩን መስረቃቸውም ተነግሯል።
እንደ ፖሊስ ገለጻ፤ ሌቦቹ በሚሰርቁበት ጊዜ የአሚያዋር መንደር ነዋሪዎች ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት የተሰራውን እና አሁን ላይ አገልግሎት መስጠት ያቆመውን አሮጌ የብረት ድልድይ የመንግስት ባለስልጣናት እንዲፈርስ የወሰኑ መስሏቸው ነበር።
ምክንያቱም የመንደሩ ነዋሪዎች ድልድዩ እንዲነሳላቸው ከዚህ ቀደም ለመስኖ ቢሮ ማመልከቻ አስገብተው እንደነበር አንድ የመንደሩ ነዋሪ ተናግረዋል።
ጋንዲ ቻውድሃሪ የተባለ የ29 ዓመቱ የመንደሩ ነዋሪ "ከባድ ማሽነሪዎችን እና የጋዝ መቁረጫ ይዘው መጡ ሰዎች ድልድዩን ለማፍረስ ለሁለት ቀናት መስራታቸውን አስታውቋል።
“የአካባቢው ነዋሪዎች ስለ ማንነታቸው ጠይቀዋቸው ነበር” ያለው ጋንዲ ድልድዩን ለማፍረስ በመስኖ ቢሮ የተቀጠሩ መሆናቸውን እንደነገሯቸው ገልጿል።
ፖሊስ በበኩሉ “ዘራፊዎቹ የህዝብ ንብረት አውድመዋል፣ ድልድይ ሰርቀዋል” ያለ ሲሆን፤ “ከዘረፋ ከቡድኑ አባላት መካከል የተወሰኑትን ለይተናል፣ የተወሰኑት ደግሞ እስካሁን ክትትል እየተደረገባቸው ነው” ብሏል።
የብረት ቁርጥራጮችን መሸጥ በህንድ ውስጥ ትርፋማ ንግድ ስራ እየሆነ መምጣቱ የተነገረ ሲሆን፤ በቶሎ ለመበልጽግ ከሕዝብ ንብረት ላይ የብረት ዕቃዎችን መስረቅ እና መሸጥ እየተለመደ መጥቷል።