የክሪስታል ፓላሱ ጆርዳን አየው እና የኒውካስትሉ ጉሜሬሽ ብዙ ጥፋት የተፈጸመባቸው ተጫዋቾች ሆነዋል
የእንግሊዝ ዳኞች ለቡካዮ ሳካ ጥበቃ እንዲያደርጉ አርሰናል ጠየቀ፡፡
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በአውሮፓ ካሉ የእግር ኳስ ክለብ ጨዋታዎች ውስጥ በአንጻራዊነት ፉክክር እንደሚበዛበት ይገለጻል፡፡
ውድድሩን ከባድ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች መካከልም በተጫዋቾች ላይ የሚፈጸሙት ጥፋቶች ሲሆኑ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2023 ዓመት ውስጥ በአንድ ጨዋታ በአማካኝ 20 ጥፋቶች ፈጸሙበታል፡፡
በዚሁ ተመሳሳይ ዓመት ውስጥ ብዙ ጥፋቶች ተፈጽመውብኛል ያለው አርሰናል ለእንግሊዝ እግር ኳስ ዳኞች አቤቱታ ማስገባቱን ስካይ ስፖርት ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ የክለቡ የፊት መስመር ተጫዋቹ እንግሊዛዊው ቡካዮ ሳካ 87 ጊዜ ጥፋቶች ተፈጽመውበታል ያለ ሲሆን ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል ሲል አስታውቋል፡፡
ከቡካዮ ሳካ በተጨማሪም የክሪስታል ፓላሱ ጆርዳን አየው በፕሪሚየር ሊጉ 112 ጥፋቶች የተፈጸመበት ሲሆን የኒውካስትሉ ጉሜሬሽ ደግሞ በ92 ጥፋቶች ከአንደኛ እስከ ሶተኛ ደረጃ ያለውን ይዘዋል፡፡
አርሰናል እንዳለው ከሆነ በቡካዮ ሳካ ላይ ጥፋት በፈጸሙ የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾ ላይ ተገቢው ቅጣት እንዳልተላለፈባቸው እንደሚያምንም አስታውቋል፡፡
የዘንድሮ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ማን ያነሳልʔ
የ22 ዓመቱ እንግሊዛዊ ቡካዮ ሳካ በተደጋጋሚ በሚፈጸምበት ጥፋቶች ምክንያት ክለቡ ውጤት እንዳያመጣ እና ተጫዋቹ በጊዜ ተቀይሮ እንዲወጣ እያደረገው ነው ብሏል፡፡
ተጫዋቹ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ለአርሰናል ያስቆጠረው ጎል አንድ ብቻ ሲሆን በቡካዮ ሳካ ላይ የሚፈጸሙ ጥፋቶች አሰልጣኙ ሚካኤል አርቴታ ሳይቀር ቢጫ ካርድ እንዲያይ ምክንያት እንደሆኑም ተገልጿል፡፡
አርሰናል ፕሪሚየር ሊጉን በ40 ነጥቦት በአራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ሊቨርፑል በ45 ነጥብ አስተን ቪላ በ42 ነጥብ እንዲሁም የአምናው አሸናፊ ማንችስተር ሲቲ በ40 ነጥብ ከአንደኛ እስከ ሶተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡