አርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ ወደ ድል ተመልሰዋል
መድፈኞቹ ወልቭስን አሸንፈው ወደ ፕሪሚየር ሊጉ አምሪነት ሲመለሱ ሲቲ ቼልሲን በመርታት ለኤፍኤ ካፕ ፍጻሜ ደርሷል
ማንቸስተር ዩናይትድ በኤፍኤ ካፕ ለፍጻሜ ለመድረስ ከኮቬንትሪ ጋር ዛሬ ይጫወታል
አርሰናል ወደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መሪነት ዳግም ተመልሷል።
የሚኬል አሬታ ቡድን በፕሪሚየር ሊጉ በአሶቶንቪላ፤ በሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ደግሞ በባየር ሙኒክ ከደረሰበት ሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ትናንት ምሽት ወልቭስን 2 ለ 0 አሸንፏል።
በሊያንድሮ ትሮሳርድ እና ማርቲን ኦዲጋርድ ጎሎች ከሜዳው ውጭ ሶስት ነጥብ ይዞ የተመለሰው አርሰናል በ74 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።
የ33ኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታውን የፊታችን ሀሙስ ከብራይተን ጋር የሚያደርገው ማንቸስተር ሲቲ በ73 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
የፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን በሳንቲያጎ በርናባው ከሻምፒዮንስ ሊጉ ከተሰናበተ በኋላ ትናንት በኤፍኤ ካፕ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ቼልሲን 1 ለ 0 በመርታት የፍጻሜው ተፋላሚ መሆኑን አረጋግጧል።
በዌምብሌይ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ በርናርዶ ሲልቫ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ጎል አስቆጥሯል።
ለሁለት ተከታታይ አመታት የሶስትዮሽ ዋንጫ ለማንሳት የሚያደረገው ትግል ባለፈው ረቡዕ በሪያል ማድሪድ የተገታበት ማንቸስተር ሲቲ፥ የኤፍኤ እና ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን የማንሳት እድሉ ከፍ ያለ ነው።
ዛሬ 11 ስአት ከ30 የሚደረገው የኮቬንትሪ እና ማንቸስተር ዩናይትድ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ የሲቲን የኤፍኤ ካፕ የፍጻሜ ተጋጣሚ ይለያል።
ከኮቬንትሪ ጋር በተገናኘባቸው 15 ጨዋታዎች (ሁሉም ውድድሮች) 13 ጊዜ ያሸነፉት ቀያዮቹ ሰይጣኖች በዌምብሌዩ ፍልሚያ ካሸነፉ የከተማ ተቀናቃኞቹ በፍጻሜው ይፋለማሉ።
አርሰናል ቀሪ አምስት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎቹን ከቼልሲ፣ ቶተንሃም፣ በርንማውዝ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ኤቨርተን ጋር ያደርጋል።
ማንቸስተር ሲቲ በበኩሉ ከብራይተን፣ ኖቲንግሃም ፎረስት፣ ወልቭስ፣ ፉልሃም፣ ቶተንሃም እና ዌስትሃም ጋር ተጫውቶ የሚያስመዘገበው ውጤት የሊጉን ዋንጫ ለተከታታይ አመታት ማንሳቱን ይወስናሉ።