የቀድሞው የባርሴሎና ተጫዋች አዳዲስ ፋሽን የመከተል ልምድ እንዳላቸው ይነገራል
የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ቅንጡ ሰአት አድርገው ታይተዋል።
ጋርዲዮላ ክለባቸው በሻምፒዮንስ ሊጉ የመጀመሪያ የሩብ ፍፃሜ ፍልሚያ በሳንቲያጎ በርናባው ሪያል ማድሪድን ሲገጥም ነው ቅንጡ ሰአት አድርገው የታዩት።
ቲኤንቲ ስፓርትን ጠቅሶ ሲኤንኤን እንደዘገበው የጋርዲዮላ ሰአት ዋጋ 1 ነጥብ 26 ሚሊየን ዶላር (ከ71 ሚሊየን ብር በላይ) ነው።
የስዊዘርላንዱ "ሪቻርድ ሚል" ሰአት ሰሪ ኩባንያ ለጋርዲዮላ የሰራውን አይነት ሰአት ያመረተው እስካሁን 50 ብቻ ነው ተብሏል።
በልዩ ዲዛይን የተሰራው ቅንጡ ሰአት በጣም ቀላሉ ሰአት መሆኑም ነው የተዘገበው።
እስከነማሰሪያው 18 ነጥብ 83 ግራም (4 ኤ4 ወረቀት) የሚመዝነው ሰአት ዋጋው ግን እጅግ ከባድ ነው።
የ"ሪቻርድ ሚል" ሰአት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራው 22 ጊዜ የግራንድ ስላም የቴኒስ ሻምፒዮን የሆነው ራፋይል ናዳል አድርጎት እንዲጫወት ነው።
ቅለቱ ላይ በትኩረት የተሰራበትን ሰአት ጋርዲዮላ በሳንቲያጎ በርናባው አድርገው መታየታቸው ትኩረት ስቧል።
መረጃዎች ግን ስፔናዊው አሰልጣኝ ከባርሴሎና ተጫዋችነት ዘመናቸው አንስቶ ቄንጠኛና ፋሽን ተከታይ መሆናቸውን ያመላክታሉ።
ማንቸስተር ሲቲን በ2016 ከያዙ በኋላ ስኬታማ ጉዟቸው ወደ ካዝናቸው ያስገባላቸው ሀብትም 71 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ሰአት ቢገዙ የሚያስደንቅ ጉዳይ አይመስልም።
ፔፕ ጋርዲዮላ በማንቸስተር ሲቲ በአመት 20 ሚሊየን ፓውንድ የሚከፈላቸው ሲሆን አጠቃላይ ሀብታቸውም ከ100 ሚሊየን ፓውንድ እንደሚደርስ ይገመታል።
ከአትሌቲኮ ማድሪድ በአመት 30 ሚሊየን ፓውንድ የሚያገኙት ዲያጎ ሲሞኔ ጋርዲዮላን በመብለጥ የአለማችን ሀብታሙ የእግርኳስ አሰልጣኝ መሆናቸው ይታወቃል።