ሊቨርፑል ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር በኦልትራፎርድ የሚያደርገው ፍልሚያም በዋንጫው ፉክክር ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል
በአለማቀፍ ጨዋታዎች ምክንያት ተቋርጦ የቆየው የ2023/24 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀመራል።
አርሰናል፣ ሊቨርፑልና ማንቸስተር ሲቲ 10 ጨዋታዎች ብቻ በቀረው ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ለማንሳት እየተፎካከሩ ነው።
መድፈኞቹ ከቀያዮቹ በእኩል 64 ነጥብ በጎል ልዩነት በመብለጥ ሊጉን እየመሩ ነው፤ የፔፕ ጋርዲዮላው ሲቲ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዘንድሮውን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ለማንሳት በሚደረገው ፉክክር ሻምፒዮኑን ይወስናሉ ያላቸውን አምስት ጨዋታዎች ይፋ አድርጓል።
ማንቸስተር ሲቲ ከአርሰናል
ነገ በኢትሃድ ምሽት 12 ስአት የሚደረገው ጨዋታ የሊጉን ሻምፒዮን ለመወሰን ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል።
በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያው የውድድሩ አጋማሽ (በጥቅምት ወር) በኤምሬትስ በጋብሬል ማርቲኔሊ ብቸኛ ጎል ያሸነፉት መድፈኞቹ፥ በኮሚዩኒቲ ሺልድ ዋንጫም በመለያ ምት ማሸነፋቸው ይታወሳል።
የሚኬል አርቴታ ቡድን ያለፉትን ስምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች አሸንፏል።
ሲቲ በበኩሉ ባለፉት 22 ጨዋታዎች (ሁሉም ውድድር) አልተሸነፈም፤ ከህዳር 2022 ወዲህም በሜዳው ሽንፈት አላስተናገደም።
ባለፈው አመት የሶስትዮሽ ዋንጫ ያሳካው የፔፕ ጋርዲዮላው ቡድን በነገው የኢትሃድ ጨዋታ የሚያሸንፍ ከሆነ ለአራተኛ ተከታታይ አመት ፕሪሚየር ሊጉን የማንሳት እድሉን ያሰፋል።
ማንቸስተር ሲቲ ከአስቶን ቪላ
ሲቲ ከአርሰናል ጋር ከተጫወተ ከሶስት ቀናት በኋላ በሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎውን ለማረጋገጥ እየታገለ ከሚገኘው አስቶንቪላ ጋር ይጫወታል።
29 ጨዋታዎችን አድርጎ በ56 ነጥብ አራተኛ ደረጃን የያዘው አስቶን ቪላ፥ በ28 ጨዋታ 53 ነጥብ ያስመዘገበው ቶተንሃም ዛሬ ሉተን ታውንን ካሽነፈ ደረጃውን ሊነጥቀው ይችላል።
የኡናይ ኢምሪ ቡድን በታህሳስ ወር በቪላ ፓርክ ሲቲን በሊዮን ቤሊይ የ74ኛ ደቂቃ ጎል ማሸንፉ ይታወሳል። ሲቲ ከዚህ ጨዋታ በኋላ አንድም ጨዋታ አለመሸነፉ አስቶን ቪላ በኢትሃድ ሊፈተን እንደሚችል ያሳያል።
ማንቸስተር ዩናይትድ ከሊቨርፑል
ሊቨርፑል በኤፍኤ ዋንጫው የሩብ ፍጻሜ ፍልሚያ በተቀናቃኙ ማንቸስተር ዩናይትድ የደረሰበትን የ4 ለ 3 ሽንፈት በፕሪሚየር ሊጉ ለመበቀል ወደ ኦልትራፎርድ ያመራል።
ቀያዮቹ የአሰልጣኝ የርገን ክሎፕን ስንበት አይረሴ ለማድረግ የፕሪሚየር ሊግ እና ዩሮፓ ሊግ ዋንጫዎችን ለማንሳት ይጫወታሉ።
ከ2021 ወዲህ በኦልትራፎርድ ያላሸነፈው ሊቨርፑል 20ኛ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫውን አንስቶ ከዩናይትድ ጋር ለመስተካከል ከዘጠኝ ቀናት በኋላ የሚደረገው ጨዋታ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ይገመታል።
ቶተንሃም ከአርሰናል
አርሰናል በ1971 እና 2004 የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ በኋይት ሃርት ሌን የከተማ ተቀናቃኙን ቶትንሃም አሸንፏል።
ከ20 አመት በፊት ምንም ጨዋታ ሳይሸነፉ ፕሪሚየር ሊጉን ካነሱ በኋላ ከሊጉ ሻምፒዮንነት የራቁት መድፈኞቹ ካለፉት ስድስት የሰሜን ለንደን ፍልሚያዎች የተሸነፉት በአንዱ ብቻ ነው፤ በዚህ የውድድር አመት በኤምሬትስ የተደረገው ጨዋታ 2 ለ 2 መጠናቀቁም ይታወሳል።
አውስትራሊያዊው አንጌ ፖስቴኮግሉ ከያዙት በኋላ በማጥቃት ላይ የተመሰረተ እግርኳስ የሚጫወተው ቶተንሃም በሊጉ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎውን ለማረጋገጥ የሚያደርገው ጨዋታ ለከተማ ተቀናቃኙ ቀላል ይሆናል ተብሎ አይገመትም።
አስቶንቪላ ከሊቨርፑል
ቀያዮቹ በመስከረም ወር በአንፊልድ 3 ለ 0 ቢረቱም በቪላ ፓርኩ ፍልሚያ ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።
ጀርመናዊው አሰልታኝ የርገን ክሎፕ በቪላ ፓርክ አራተኛ ተከታታይ ድላቸውን ለማስመዝገብ የሚያደርጉት ጨዋታ በሊጉ የሻምፒዮንነት ፉክክር ተጠባቂ ከሆኑ ጨዋታዎች ተመድቧል።
ቪላ በ2020 ሊቨርፑልን 7 ለ 2 ካሸነፈ በኋላ ቀያዮቹን መርታት አልቻለም። ከአራት አመት በኋላ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት የተቃረበው የመርሲሳይዱ ክለብ ለ2020ው አይነት አሳፋሪ ሽንፈት ዝግጁ አይመስልም።
ወሳኟ ቀን
የማይገመቱ ውጤቶች የሚመዘገቡበት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከላይ የተጠቀሱት ወሳኝ ፍልሚያዎች የዋንጫውን ባለቤት ካልለዩ ግንቦት 19 2024 በተመሳሳይ ምሽት 12 ስአት የሚደረጉ ጨዋታዎች ይጠበቃሉ።
አርሰናል በኤምሬትስ ኤቨርተንን፤ ማንቸስተር ሲቲ በኢትሃድ ዌስትሃምን፤ ሊቨርፑል በአንፊልድ ወልቭስን ይገጥማሉ።