የመጀመሪያዋ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዲጄ ስራ ጀምራለች
በአሜሪካ ኦሪገን የሚገኝ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ነው የቻትጂፒቲ ቴክኖሎጂ የምትጠቀም ዲጄ ስራ ያስጀመረው
“አሽሊ” የተሰኘችው የሙዚቃ አጫዋች (ዲጄ) አድማጮችን በማዝናናት ላይ ናት
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ በብሮድካስት ሬዲዮ ዘርፍም አሻራውን ማኖር ጀምሯል።
በአሜሪካ ፖርትላንድ ኦሪገን የሚገኘው የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ (ላይቭ 95 ነጥብ 5) የመጀመሪያዋን ሮቦት የሙዚቃ አጫዋች ወይም ዲጄ ወደ ስራ አስገብቷል።
ሙዚቃዎችን በሚገባ አዘጋጅታ እያከታተለች የምትጋብዘው፤ በየመሃሉም መረጃ እየሰጠች ከአድማጮቿ ጋር ቆይታ የምታደርገው ዲጄ “ኤአይ አሽሊ” ትሰኛለች።
ሮቦት ዲጄዋ የዚሁ ሬዲዮ ጣቢያ ጋዜጠኛ ከሆነችው አሽሊ ዚንጋ ድምጽ ወስዳለች።
አሽሊ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ምትኳን ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ ስታስተዋውቃትም ቁርጥ እሷን ሆና አግኝታታለች።
“እናም ከዚህ በኋላ እረፍት ማድረግ እችላለሁ ኤአይ አሽሊ እኔን ተክታ ታዝናናችኋለች” ብላለች የቀጣይ እንጀራዋ አደጋ ላይ የወደቀባት የምትመስለው አሽሊ።
የሬዲዮ ጣቢያው በትዊተር ገጹ ላይ ባጋራው የመጀመሪያው የአሽሊ የቀጥታ ስርጭት ቆይታም ድምጿ የሰው እንጂ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አይመስልም።
ቻትጂፒቲ በቅርቡ ያስተዋወቀውን “ጂፒቲ 4” የተሰኘ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የምትጠቀመው አሽሊ በየቀኑ የሙዚቃ ማጫወት ስራዋን ቀጥላለች።
ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች የመዝናኛ ዜናዎችን በመፈለግም ወደ አድማጮቿ ታደርሳለች መባሉን ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘግቧል።
ይህ ሙከራ ታሪካዊ ነው ያለው የኤፍ ኤም ጣቢያው፥ ዋናዋ አሽሊ (አሽሊ ዛንጋ) ስራዋን እንደማታጣ ቃል ገብቷል።
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሰው ልጅን ህይወት የማቅለሉን ያህል ፈተናዎቹም ቀላል አልሆኑም።
ከ300 ሚሊየን በላይ ሰዎች በዚሁ ቴክኖሎጂ መምጣት ምክንያት ስራቸውን ሊያጡ እንደሚችሉም በቅርቡ ይፋ የተደረገ ጥናት ማመላከቱ ይታወሳል።