የአሳድ ዘመዶች ከሊባኖስ ለመውጣት ሲሞክሩ በቁጥጥር ስር ዋሉ
የቀድሞው የሶሪያ ፕሬዝዳንት ቤተሰቦች በህገወጥ መንገድ ሊባኖስ ገብተው በሀሰተኛ ፓስፖርት ወደ ግብጽ ሊጓዙ ነበር ተብሏል
አሳድ ወደ ሞስኮ በኮበለሉበት እለት ብቻ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሶሪያውያን ወደ ሊባኖስ ገብተዋል
የቀድሞው የሶሪያ ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ዘመዶች ከሊባኖስ ለመውጣት ሲሞክሩ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነገረ።
የአሳድ አጎቶች፣ ሚስቶችና ልጆቻቸው በሊባኖስ በኩል አድርገው ግብጽ ለመግባት ሲሞክሩ መያዛቸውን አሶሼትድ ፕረስ የሊባኖስ ምንጩቹን ጠቅሶ አስነብቧል።
የቀድሞው የሶሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪፋት አሳድ ልጅ ዱራይድ አሳድ ሚስትና ልጃቸው ሊጃቸው ሊባኖስ የገቡት በህገወጥ መንገድ ነው ተብሏል።
በሀሰተኛ ፓስፖርት ወደ ግብጽ በአውሮፕላን ለመጓዝ ሲሞክሩም በሊባኖስ የደህንነት ሰራተኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።
ሪፋት አሳድ ግን በትናንትናው እለት በትክክለኛ ፓስፖርቱ ከሊባኖስ መውጣቱ የተነገረ ሲሆን፥ ቤሩት ጉዞውን ማስቆም አልቻለችም ተብሏል።
የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ሪፋት አሳድ በሀማ ተፈጽሟል በተባለ የዘር ማጥፋት ወንጀል በ2024 መጀመሪያ በስዊዘርላንድ ጥፋተኛ መባላቸውን ኤፒ አስታውሷል።
ሶሪያን ለ24 አመት የመሩት በሽር አል አሳድ ከሁለት ሳምንት በፊት ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ቤተሰቦቻቸውና የቅርብ ወዳጆቻቸው የሊባኖስ ታርጋ ባላቸው መኪናዎች ከሶሪያ መውጣታቸው ተነግሯል።
የአሳድ አገዛዝን በመደገፋቸው ስልጣን በጨበጠው ሃይል ጥቃት እንደሚደርስባቸው ያመኑ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሶሪያውያንም አሳድ ወደ ሞስኮ በኮበለሉበት እለት ብቻ ወደ ሊባኖስ በህገወጥ መንገድ መግባታቸው ነው የተገለጸው።
የሊባኖስ የደህንነት ተቋም ከ20 በላይ የሚሆኑ በጭካኔው የሚታወቀው የቀድሞው የሶሪያ ጦር 4ኛ ዲቪዚዮን አባላት፣ የወታደራዊ ደህንነት ባለሙያዎችና ሌሎች ለአሳድ ቅርበት የነበራቸው ከፍተኛ የጸጥታ አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል። አንዳንዶቹም የጦር መሳሪያዎቻቸውን ለመሸጥ ሲሞክሩ ነው የተያዙት።
ቤሩት የሶሪያውን የቀድሞ የደህንነት ሃላፊ ጃሚል አል ሃሰን በቁጥጥር ስር አውላ አሳልፋ እንድትሰጥ ከአለማቀፉ ፖሊስ ኢንተርፖል ደብዳቤ ደርሷታል።
የሊባኖስ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ነጂብ ሚካቲ ከዚህ ቀደም ሀገራቸው አል ሃሰንን ለመያዝ ከኢንተርፖል ጋር በትብብር እንደምትሰራ ለሬውተርስ መናገራቸው የሚታወስ ነው።