አሜሪካ አዲሱን የሶሪያ መሪ በቁጥጥር ስር ለማዋል አውጥታው የነበረውን የእስር ማዘዣ ሰረዘች
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተመራ ልዑክ ከአህመድ አልሻራ ጋር ውይይት አድርጓል
በሽር አል አሳድን የጣለው የኤቺቲኤስ አማጺ ቡድን አሁንም ከአሜሪካ የሽብርተኝነት መዝገብ የሽብር መዝገብ ውስጥ አልተሰረዘም
በአዲሱ የሶሪያ መሪ አህመድ አልሻራ ላይ አሜሪካ አውጥታው የነበረውን የእስር ማዘዣ መሰረዟን አስታወቀች፡፡
ዋሽንግተን የአማጽያን ቡድን መሪ የሆነውን አልሻራን ለያዘ የ10 ሚሊየን ዶላር ሽልማት ለመስጠት ቃል ገብታ ነበር፡፡
አህመድ አልሻራ የእስር ማዘዣው የተነሳለት ከአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ጋር በተደረገ ስምምነት ነው፡፡
በትላንትናው እለት በአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባርባራ ሌፍ የተመራ ልዑካን ቡድን በደማስቆ ከአልሻራ ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ የሶሪያን የሽግግር ሂደት ለመደገፍ እና የአይኤስን እንቅስቃሴ ሙሉለሙሉ ለማጥፋት ከቀጠናው አጋሮች ጋር በትብብር መስራት እንደሚገባ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር የልዑካን ቡድኑ በሶሪያ ከሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች እና ከተለያዩ ማህበረሰቦች ክፍሎች ጋር ስለ ሀገራቸው የወደፊት ራዕይ እና አሜሪካ እንዴት ልትረዳቸው እንደምትችል መነጋገሩን ተናግረዋል።
ከአስርተ አመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የአሜሪካ ልዑካን ቡድን በደማስቆ መገኘት አዲስ በሚመሰረተው መንግስት ላይ አውሮፓ ፣ አሜሪካ እና የአረብ ሀገራት መፍጠር የሚፈልጉትን ተጽዕኖ ያመላክታል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በቅርቡ የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ የጀርመን ፣ የብሪታንያ እና ፈረንሳይ ልዑካን ወደ ደማስቆ በማቅናት ከአዲሱ አስተዳደር ጋር በቅርበት መስራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ሀገሪቱን መልሶ ለመገንባት ፣ ኢኮኖሚያው እና ወታደራዊ ድጋፍን ለማድረግ የጸጥታ ሁኔታዎች ላይ በተለያዩ መንገዶች ለመደገፍ ቃል ገብተዋል፡፡
ምዕራባውያን በሶሪያ ሀይማኖታዊ መንግስት እንዳይመሰረት አዲሱን አስተዳደር ለማሳመን ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ ያለው የቢቢሲ ዘገባ፤ ኤችቲኤስ የተባለው ቡድን እስካሁን የሽብርተኝነት ፍረጃው ያልተነሳለት የአስተዳደሩ መንግስታዊ መዋቅር ላይ እርግጠኛ ለመሆን ሊሆን ይችላል ብሏል፡፡
ዋሽንግተን በደማስቆ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን ከማንሳቷ በፊት በቅድመ ሁኔታነት ካስቀመጠቻቸው ነጥቦች መካከል ይሄው የሀይማኖታዊ መንግስት ጉዳይ አንዱ ነው፡፡