ኢራን በሶሪያ ውስጥ ቀውስ ከመፍጠር እንድትቆጠብ የሶሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስጠነቀቁ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሳድ ሀሰን ቴሄራን የደማስቆን ሉአላዊነት እና የዜጎችን ፍላጎት እንድታከብር ጠይቀዋል
በ13 አመቱ የሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ኢራን የበሽር አላሳድ መንግስት ዋነኛ ደጋፊ ሆና መቆየቷ ይታወሳል
ኢራን በሶሪያ ውስጥ ቀውስ እና ትርምስ ከመፍጠር እንድትቆጠብ የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሳድ ሀሰን አስጠነቀቁ፡፡
አዲስ እየተቋቋመ በሚገኘው የሽግግር መንግስት ውስጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አሳድ ሶሪያውንያን የተሻለ የፖለቲካ ስርአትን እና ሀገርን ለመገንባት ጥረት ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ በይፋዊ የኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት የሶሪያውያን ዜጎች ፍላጎት እና ሉዐላዊነት እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡
የኢራን ሀይማኖታዊ መሪ አያቶላ አሊ ካሚኒ የሶሪያ ወጣቶች ሀገሪቱ የገጠማትን የደህንነት ችግር ያቀነባበሩትን አካላት በቁርጠኝነት እንዲጋፈጧቸው በቴሌቪዥን የተላለፈ ንግግር አድርገዋል፡፡
ሀይማኖታዊ መሪው አክለውም "በሶሪያ ውስጥ ጠንካራ ቡድን እንደሚፈጠር እናምናለን፤ ምክንያቱም ዛሬ የሶሪያ ወጣቶች ምንም የሚያጡት ነገር የለም፤ ትምህርት ቤቶቻቸው፣ ዩኒቨርስቲዎች፣ ቤቶች እና መንገዶቻቸው አስተማማኝ አይደሉም" ብለዋል፡፡
የአዲሱ የሶሪያ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሳድ ሀሰን በመልዕክታቸው “ኢራን ትርምስ ለመፍጠር የምታደርገውን ጥረት እናውቃለን፤ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያዘ በመሪዋ በኩል ያስተላለፈችውን የአመጻ ጥሪ ተከትሎ ችግር ቢፈጠር ተጠያቂ ትሆናለች” ነው ያሉት፡፡
ከአስርት አመታት የአንድ ቤተሰብ የአምባገነን አገዛዝ በኋላ ሶሪያውያን የራሳቸውን አስተዳደር እና መንግስት ለመመስረት በሽግግር ላይ ይገኛሉ፡፡
ሚኒስትሩ ይህን ሂደት ለማደናቀፍ ሽብር እና ፍርሀትን ለመንዛት የሚደረግ ጥረት ድጋሚ ጦርነትን ማወጅ ነው ሲሉ ተቃውመዋል፡፡
የበሽር አላሳድ መንግስትን ለመጣል ለ13 አመታት በተደረገው ትግል ኢራን እና ሩስያ ከአልአሳድ መንግስት ጎን በመቆም ተዋግተዋል፡፡
ባለፉት አመታትም ቴሄራን ብቻዋን የመንግስትን ጦር ለማጠናከር በቢሊየን ዶላር የሚገመት ገንዘብ ፈሰስ ከማድረግ ተሻግራ የአብዮታዊ ዘብ ጦሯን በሶሪያ አሰማርታ እንደነበር ይታወቃል፡፡
ከሄዝቦላህ እና የሀማስ ቡድኖች ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አቅም መዳከም ባለፈ የበሽር አልአሳድ መንግስት መውደቅ ኢራን በቀጠናው ያላትን ተጽዕኖ እንደሚቀንሰው እየተነገረ ይገኛል፡፡