ኪንሻሳ በኮንጎ ወንዝ ላይ የምትገኝ 15 ሚሊዮን ሰዎች መኖሪያ ከተማ መሆኗ ይታወቃል
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዋና ከተማ ኪንሻሳ ለዓመታት ታይቶ በማይታወቅ የጎርፍ አደጋ ከ120 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡
ለሰአታት በጣለው ከባድ ዝናብ በርካታ ቤቶች የፈረሱ ሲሆን በመሀል ከተማ የሚገኙት ዋና ዋና መንገዶች በውሃ ተሞልተው መንገዶች ተዘግቷል፡፡
ዋና ከተማዋ ኪንሻሳን ከሀገሪቱ ዋና ወደብ ማታዲ ጋር የሚያገናኘው የ ኤን-1 አውራ ጎዳና በውሃ ተጥለቅልቆ ለጊዜው አገልግሎት መስጠት ካቆሙ መንገዶች አንዱ ነው፡፡
ከሞቱት መካከል ብዙዎቹ የመሬት መደርመስ አደጋ ባጋጠማቸው ኮረብታማ ስፍራዎች የሚኖሩ ሲሆኑ ፤ የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ ይችላል ተብሏል፡፡
አጃንስ ፍራንስ ፕረስ ያነጋገረውና የከፋ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች አንዱ ነዋሪ የሆነው ብላንቻርድ ምቩቡ፣ “በዚህ መጠን የጎርፍ መጥለቅለቅ አይተን አናውቅም” ብሏል፡፡
"እኔ ተኝቼ ነበር፤ በቤቱ ውስጥ ውሃ መፍሰሱ ይሰማኝ ነበር፤ ይህ አስደንጋጭ አደጋ ነው ፤ በቤቱ ውስጥ ያለውን ንብረታችንን በሙሉ አጥተናል ፤ ምንም ሊድን አልቻለም" ሲልም አክሏል ብላንቻርድ ምቩቡ፡፡
አሳዛኛኙን አደጋ ተከትሎ የሀገሪቱ መንግስት ለሶስት ቀናት የሚቆይ ብሄራዊ ሀዘን አውጇል፡፡
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዣን ሚሼል ሳማ ሉኮንዴ የመንግስት ልዑካን ቡድንን በመምራት በኪንሻሳ ተገኝተው የአደጋውን መጠን ለመገምገም ችለዋል፡፡
መንግስት ተጨማሪ አስከሬን ፍለጋ ላይ አስፈላጊውን ስራ እየሰራ መሆኑም ተናግረዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለአሜሪካ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ በዋሽንግተን የሚገኙት የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሺስኬዲ የአየር ንብረት ለውጥን ለትልቅ የጎርፍ አደጋ ዋነኛ ምክንያት መሆኑንና ዓለም ለመፍትሄው መትጋት እንዳለበት ትናንት ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር በነበራቸው ውይይት ማንሳታቸው ይታወቃል፡፡
"ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጫና ውስጥ ነው ያለችው፤ ነገር ግን አሁንም በበቂ ሁኔታ አልተሳማችም እንዲሁም አልተደገፈችም " ሲሉም ነበር ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሺስኬዲ ለብሊንከን የነገሯቸው።
ለብክለት ተጠያቂ የሆኑት ሀገራት በችግር ላይ ያሉትን መርዳት አለባቸውም ብለዋል።
የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ እንዳሉት ፕሬዝዳንቱ በአደጋው ምክንያት የአሜሪካ ቆይታቸውን ሊያሳጥሩት ይችላሉ።
እንደ ፈረንጆቹ ህዳር 2019 በኪንሻሳ ወደ 40 የሚጠጉ ሰዎች በጎርፍ አደጋ እና በመሬት መንሸራተት መሞታቸው አይዘነጋም፡፡
ኪንሻሳ በኮንጎ ወንዝ ላይ የምትገኝ 15 ሚሊዮን ሰዎች መኖሪያ ከተማ ናት፡፡