እሳተ ገሞራ መከሰቱን ተከትሎ በርካታ የዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዜጎች ወደ ሩዋንዳ እየተሰደዱ ነው
የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ አጎራባች አገር ሩዋንዳ ቤታቸውን ጥለው በመሸሽ ላይ ናቸው
የእሳተ ገሞራው ምልክቶቹ የታዩት በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል በምትገኘው ጎማ ከተማ ነው
በሰሜናዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ እሳተ ገሞራ መከሰቱን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ የሃገሪቱ ዜጎች መኖሪያ ቀያቸውን ለቀው እየወጡ ነው፡፡
እሳተ ገሞራው በሰሜናዊ የሃገሪቱ አካባቢ ጎማ ከተማ ያጋጠመ ነው፡፡
እሳተ ገሞራው እንዲሚከሰት ምልክቶች አስቀድመው ታይተው ነበር ያለው ሲጂቲኤን አፍሪካ ነዋሪዎች ከአደጋው ለማምለጥ በሚል የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ ጎረቤት ሃገር ሩዋንዳ እየተሰደዱ መሆኑን ዘግቧል፡፡
ሩዋንዳም ስደተኞቹን ተቀብላ ለማስተናገድ ዝግጅት መጀመሯንም ነው ዓለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛዎች የዘገቡት፡፡
ከአንድ ሳምንት በፊት የጎማ እሳተ ገሞራ ጥናት ማዕከል በአካባቢው አደጋ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቆም ነበር ተብሏል።
በጎማ ከተማ አቅራቢያ ካለው ኒራጎንጎ ተራራ ላይ ከትናንት ጀምሮ የታየው የእሳተ ገሞራው ምልክቶች ነዋሪዎቹን ስጋት ላይ ጥሏል።
ከዚህ ተራራ ላይ መነሻውን ያደረገ እሳተ ገሞራ በፈረንጆቹ 2002 ዓመት ተመሳሳይ አደጋ ተከስቶ የ100 ሰዎች ህይወት አልፎ እንደነበር ተገልጿል።
የአገሪቱ ፕሬዘዳንት ፌሊክ ሺስኬዲ በአውሮፓ እያደረጉት ያለውን የእርዳታ ማሰባሰብ ፕሮግራም ዛሬ አቋርጠው ወደ ኪንሻሳ እንደሚመለሱ ይጠበቃል።
በአካባቢው ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን ህጻናት እና ሴቶች እግራቸው ወዳመራቸው አካባቢዎች በፍጥነት አካባቢያቸውን በመልቀቅ ላይ መሆናቸውን ዘገባው አክሏል።
ጎማ ከተማ በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ካሉ ከተሞች ትልቁ ከተማ ሲሆን በመንግስታቱ ድርጅት ስር ያለው ሰላም አስከባሪ ጦር እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶች ዋና መቀመጫም ናት።