የእሳተ ገሞራ ፍንዳታው ባሳለፍነው ቅዳሜ በናይራጎንጎ ተራራ ላይ ነው የተከሰተው
በምስራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጎማ ከተማ አቅራቢያ ባጋጠመው የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 32 መድረሱን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የእሳተ ገሞራ ፍንዳታው በናይራጎንጎ ተራራ ላይ ባሳለፍነው ቅዳሜ ያጋጠመ ሲሆን፤ በአደጋው ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ባለስልጣናቱ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በእሳተ ገሞራ ፍንዳታው ህይወታቸውን ካጡ ሰዎች መካከል 9 ሰዎች የእሳተ ገሞራው ቅልጥ አለት (ላቫ) ቤታቸው ላይ በማረፉ ተቃጥለው ህወታቸው ማለፉ ነው የተገለጸው።
አምስት ሰዎች ደግሞ በመቀዝቀዝ ላይ ባለ ላቫ በኩል በማለፍ ላይ እያሉ በአካባቢው በነበረ መርዛማ ጭስ አማካኝነት ህወተጨውን አጥተዋል።
14 ሰዎች የእሳተ ገሞራ ፍንዳታውን በመሸሽ ላይ እያሉ በደረሰ የመኪና መገልበጥ አደጋ ህይወታቸው ማለፉን እና ቀሪ 4 ሰዎች ደግሞ በጎማ ከተማ ከሚገኘው እስር ቤት ለማምለጥ ሲሉ ህይወታቸው ማለፉንም የሀገሪቱ ባለስልጠናት አስታውቀዋል።
የሀገሪቱ መንግስት ልኡክ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታውን ሁኔታ እንዲሁም ሰብዓዊ ድጋፎች፣ የጤና እና ደህንነት ሁኔታው ምን እንደሚመስሉ ለመመልከት ወደ ስፍራው ማቅናቱ ተነግሯል።
በአሁኑ ወቅት ከናይራጎንጎ ተራራ አናት ላይ ወደ ጎማ ከተማ እና አጎራባች ወደ ሆኑ የከተማው አካባቢዎች የሚፈሰው ቅልጥ አለት (ላቫ) መቆሙ ታውቋል።
ባሳለፍነው ቅዳሜ የተከሰተው እሳተ ገሞራ ፣ በርካቶች የመኖሪያ ቀዬያቸውን ለቀው ወደ አጎራባች የሩዋንዳ አካባቢዎች እንዲሰደዱ ማድረጉም ይታወቃል።