በሱዳን በጎርፍ የተወሰዱ ሰዎች ቁጥር 112 ደረሰ
በጎርፉ ከ83 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶች ሲወድሙ 250 ሺህ ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል
በመስከረም ወር ተጨማሪ ዜጎች ለጎርፍ አደጋ ሊጋለጡ እንደሚችሉ ተገልጿል
በሱዳን በጎርፍ የተወሰዱ ሰዎች 112 ደርሷል።
በሱዳን ካሳለፍነው ሰኔ ወር ጀምሮ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 112 ማሻቀቡን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የዓባይ ወንዝ የውሃ መጠን በመጪዎቹ ቀናት የበለጠ ሊጨምር እንደሚችልም የገለፁት የሃገሪቱ የአደጋ መከላከል ባለስልጣናት አስጠንቅቀዋል።
ባለስልጣናቱ በዚህ ወር ብቻ ባጋጠመ አደጋ 112 ሱዳናውያን መሞታቸውንና 115 ሰዎች ደግሞ መጎዳታቸውን አስታውቀዋል።በድምሩ 84 ሺ 40 ቤቶች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል መውደማቸው እና መጎዳታቸውንም ተናግረዋል ባለስልጣናቱ።
መሠል የጎርፍ አደጋዎች ለሱዳን አዲስ አይደሉም። ክረምት በመጣ ቁጥርም ያጋጥማል። ሆኖም ዘንድሮ በ1940ዎቹ ካጋጠመውና የከፋ ነበር ከተባለለት የበለጠ የጎርፍ አደጋ ማጋጠሙ ነው የተነገረው።
አደጋው ካለፉት ሁለት የክረምት ወራት ይልቅ በነሐሴ እና መስከረም ወራት ይከፋል መባሉም ብዙዎችን አስግቷል።
የጎርፍ አደጋው በስድስት ግዛቶች እየከፋ የመጣ ሲሆን የሀገሪቱ ወታደራዊ መንግስትም በነዚህ ግዛቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።
ናይል፣ ዋይት ናይል፣ ኮርዶፋን፣ ዳርፉር እና ካሳላ ግዛቶች በጎርፍ አደጋው ክፉኛ ተጎድተዋል ተብሏል፡፡
እስካሁን ባለው የጎርፍ አደጋ ከ250 ሺህ በላይ ዜጎች ከመኖሪያ ቤታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን በቀጣዮቹ ሳምንታት ተጨማሪ ጉዳት ሊከሰት እንደሚችል ተጠቅሷል።