የጎርፍ አደጋው በምዕራባዊ የአውሮፓ ሀገራት የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ ነው
በምዕራብ አውሮፓ ሀገራት በደረሰ የጎርፍ አደጋ ከ48 በላይ ሰዎች ሕይወት ማፉ ተገለጸ።
በጀርመን በደረሰው የጎርፍ አደጋው የ42 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፤ በርካቶች እስካሁን የገቡበት እንዳልታወቀ እና የማፈላግ ስራ እተካሄደ መሆኑም ታውቋል።
የጎርፍ አደጋው በተለይም በረሂንላንድ ፐላቲናቴ እና በሰሜን ርሂን ዌስትፋሊያ ከባድ ጉዳት ማድረሱ የተገለጸ ሲሆን፤ በርካታ ህንፃዎች እና ቆመው የነበሩ ተሸከርካሪዎች በጎርፍ መወሰዳቸውም ታውቋል።
የጀርመን በረሂንላንድ ፐላቲናቴ ግዛት አስተዳዳሪ ማሉ ደሬየር፤ አደጋው በጣም ከባድ እና አሳዛኝ እንደሆነ ተናረዋል።
“በጎርፍ አደጋው በርካቶች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ የጠፉ ሰዎችም አሉ፤ በርካቶች ደግሞ አሁንም በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ” ሲሉም ተናግረዋል።
ከአሜሪካው ፐሬዚዳንት ጋር ለመምከር ኒውዮርክ የሚገኙት የጀርመኗ መራሄተ መንግትስ አግላ ሜርክል በበኩላቸው፤ “አደጋው አስደንጋጭ እና አሳዛኝ ነው” ማለታቸው ተሰምቷል።
በተመሳሳይ በቤልጂየምም የጎርፍ አደጋ የደረሰ ሲሆን፤ በአደጋው የ6 ሰዎች ህይወት አልፏል፤ ሊግ ከተማ ነዋሪዎችም የከፋ የጎርፍ አደጋ ሊደርስ ስለሚችል ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ እየተደረገ ነው ተብሏል።
በኔዘርላንድም የጎርፍ አደጋው ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ የተገለጸ ሲሆን፤ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ባይደርስም በርካታ ህንፃዎች እና ተሸከርካሪዎች በጎርፍ መወሰዳቸው ተነግሯል።
የጎርፍ አደጋው በምዕራባዊ የአውሮፓ ሀገራት የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ ወንዞች ሞልተው በመፍሰሳቸው የደረሰ አደጋ ነው።