በማሊ በተፈጸሙ 3 ጥቃቶች 40 ሰዎች ተገደሉ፡፡
በማሊ በተፈጸሙ 3 ጥቃቶች 40 ሰዎች ተገደሉ፡፡
ከትናንት በስቲያ በማሊ በተፈጸሙ ሶስት የተለያዩ ጥቃቶች 9 ወታደሮችን ጨምሮ 40 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ 31 ሰዎች የተገደሉት ታጣቂዎች በማእከላዊ ማሊ በሚገኝ አንድ መንደር በፈጸሙት ጥቃት ሲሆን በመንደሩ ቤቶችን፣ እንስሳትን እና የእህል ክምሮችንም አቃጥለዋል፡፡
በዋናነት የፉላኒ ብሔረሰብ አባላት በሚኖሩበት ኦጋሳጉ መንደር አርብ ምሽት ነው ጥቃቱ የተፈጸመው፡፡ በዚሁ ስፍራ ባለፈው መጋቢት ወር በተመሳሳይ በታጣቂ ሚሊሻዎች በተፈጸመ ጥቃት 160 ሰዎች ተገድለዋል፡፡
በወቅቱ የ160 ሰዎችን መገደል ተከትሎ የማሊ መንግስት ከህዝቡ ከፍተኛ ተቃውሞ አስተናግዶ ጠቅላይ ሚኒስትር ሱሜይሉ ቡቤዬ ማይጋ ከኃላፊነት ለመነሳት ተገደዋል፡፡
የመንደሩ አስተዳዳ አሊ ኦስማን እንደገለጹት አዲሱ ጥቃት የተፈጸመው በ30 ታጣቂዎች ነው፡፡ የአካባቢው ባለስልጣናት ጥቃት ፈጻሚዎቹ በማሊ ከሚኖሩ ብሄሮች መካከል የሆኑት የዶጎን ብሔር አባላት ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከአካባቢው የሀገሪቱ ጦር ከተነሳ በኋላ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ጥቃት በመፈጸም ላይ እንደሆኑም ነው ዘ ጋርዲያን የዘገበው፡፡
ከ40 ሟቾች መካከል ዘጠኙ ወታደሮች ሲሆኑ 8 ወታደሮች በደፈጣ ጥቃት፣1 ወታደር ደግሞ በጋኦ ግዛት በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ነው የተገደሉት፡፡ ሌሎች 4 ወታደሮችም በጥቃቱ ቆስለዋል፡፡
ለሶስቱም ጥቃቶች ባለስልጣናት ጣታቸውን በዶንጎ ጽንፈኛ ሚሊሻዎች ላይ ጣታቸውን ቢቀስሩም እስካሁን ኃላፊነቱን የወሰደ አካል ግን የለም፡፡
እስላማዊ ጽንፈኛ ታጣቂዎች በሀገሪቱ ከተፈጠሩበት ከአውሮፓውያኑ 2012 ጀምሮ ማሊ ከፍተኛ አለመረጋጋት ይስተዋልባታል፡፡
ጽንፈኛ ታጣቂዎቹ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሀንን ህይወት የቀጠፉ ሲሆን በማሊ አጎራባች ሀገራት ኒጀር እና ቡርኪና ፋሶም ተዛምተዋል፡፡
የሀገሪቱ ወታደሮች ደግሞ ጽንፈኞችን ለመዋጋት የቁሳቁስ እጥረት እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡ በቀጣናው በመንሰራፋት ላይ የሚገኘውን የጽንፈኞች እንቅስቃሴ ለመከላከል 13 ሺ የተባበሩት መንግስታት ወታደሮችም በሀገሪቱ ይገኛሉ፡፡
ምንጭ፡- ዘ ጋርዲያን