በግብፅ ባለ 10 ፎቁ መኖሪያ ህንጻ ተደረመሰ
የነፍስ አድን ሰራተኞች ከማለዳ ጀምሮ በህይወት ያሉ ተጎጂዎችን ለመታደግ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ ተብሏል
በአደጋው የ8 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 29 ሰዎች መጎዳታቸው ተሰምቷል
በግብጽ ምሥራቃዊ ካይሮ በጌስር ኤል ስዌዝ አካባቢ የሚገኝ ባለ 10 ፎቅ የመኖሪያ ህንጻ በመደርመሱ የ8 ሰዎች ህይወት አለፈ፡፡
በአደጋው 29 ሰዎች ለጉዳት መዳረጋቸውም ተነግሯል፡፡
መኖሪያ ህንጻው ኦማር ቢን አል-ቀጣብ ተብሎ በሚጠራ ባቡር ጣቢያ አቅራቢያ ይገኝ የነበረ ነው፡፡
አደጋውን ተከትሎም የግብፅ ነፍስ አድን ሰራተኞች ከጠዋቱ አንስቶ ፍርስራሹ ስር በሕይወት የተረፉ ሰዎችን ለመፈለግ ጥረታቸውን ቀጥለዋል ፡፡
በስፍራው አስጊ ሁኔታዎች ይታዩ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪ የአል-ዐይን ምንጮች ተናግረዋል፡፡
የመደርመስ ምልክት መታየቱን ተከትሎም ገሚሶቹ ነዋሪዎች ስፍራውን ለቀው መውጣታቸው እንዲሁም ምርጫ ያልነበራቸው በስፍራው መቆየታቸውንም ጭምር ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት፡፡
ህንፃው ዛሬ ማለዳ መደርመሱንም ሁኔታውን ወዲያውኑ ለበላይ አካል አሳወቅን ያሉት ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
ይህን በማድረጋችን የሃገሪቱ የፀጥታ ኃይል የአደጋውን ሰለባዎች ከሞት ለመታደግ አስፈላጊውን ጥረት እያደረገ ይገኛልም ብለዋል፡፡
18 የአምቡላንስ ተሽከርካሪዎች በአከባበቢው ተሰማርተው በፍርስራሹ ስር ለተገኙና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ወደ አል-ሳላምና አይን-ሻም አጠቃላይ ሆስፒታሎች እየወሰዱ መሆናቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡